AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም
የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን በጎ ምግባርንና ግብረገብነትን በማስረጽ፣ የጥላቻ ንግግርንና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አሳሰበ።
ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር “ጠንካራ ትብብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ቃል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት በዋናነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭቶችን በጋራ ለመግታት ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ዓመታት በኋላ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት የራሳቸው መገናኛ ብዙኃን እንዲኖራቸው ሰፊ ዕድልና ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም መሠረት ከዲጂታል ሚዲያዎች ውጪ 51 የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ተፈጥረው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ካላቸው ሰፊ ተደራሽነትና ተቀባይነት አንጻር፣ በጎ ምግባርንና ግብረገብነትን በማስረጽ ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ ነው ሲሉ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ በአንዳንድ የሃይማኖት ሚዲያዎች ላይ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭቶች ስለመኖራቸው ለባለሥልጣኑ መረጃዎች ቢደርሱትም፣ እስካሁን ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ መታቀቡን ገልጸዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ችግሮቹን በውይይትና በጋራ ለመፍታት በማለም እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ሰላምና አንድነትን ማጽናት የሃይማኖት ሚዲያዎች ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያዊ መልካም ባህል ያፈነገጡና አንድነትን የሚያሻክሩ መረጃዎች እየተስተዋሉ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሐፊው፤ ይህንን እኩይ ድርጊት ለመግታት ጉባኤው ከባለሥልጣኑ ጋር በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በሥነ ምግባር የታነጸና ለሀገሩ ክብር ቅድሚያ የሚሰጥ የመገናኛ ብዙኃን ሥርዓት በሀገር ደረጃ ሊጠናከር እንደሚገባና ለዚህም ስኬት የሃይማኖት ተቋማት መሪ የመሆን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገልጸዋል።
በራሄል አበበ