AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

ዛሬ በዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሴኔጋልና ፈረንሳይ ሲገናኙ፣ ትውስታችን ወደ ኋላ ወደ እ.አ.አ. 2002 ይወስደናል።
ኮሪያና ጃፓን በጋራ ባዘጋጁት በዚያ የዓለም ዋንጫ ላይ የተፈጠረውን ተዓምር የሚረሳ የለም ፤ ያንን ታሪክ ያልተመለከተውም ቢሆን ሲሰማ መገረሙ አይቀርም።

ነገሩ እንዲህ ነበር ፤ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴኡል ከተማ እ.አ.አ. ግንቦት 31 ቀን 2002። የሴኔጋልና የፈረንሳይ የመክፈቻ ጨዋታ። በዚያን ጊዜ ፈረንሳይ የ1998 የዓለም ዋንጫ እና የ2000 የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን ነበረች።

እንደ ቲዬሪ ኦንሪ፣ ፓትሪክ ቪዬራ፣ ማርሴል ደሳይ፣ ክሎድ ማኬሌሌ፣ ሊሊያን ቱራም እና ማኑኤል ፔቲት ያሉ ልዩ ችሎታ ያላቸውን ኮከብ ተጫዋቾች ለዚህ ጨዋታ አሰልፋ ነበር። ሴኔጋል በበኩሏ ለዓለም አዲስ ነበረች።
ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ላይ እየተሳተፈች ነበር። አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው በታችኞቹ የፈረንሳይ ሊግ ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ ቢሆንም፣ በአንበሳ ልብ የተሞሉና ለሀገራቸው እስከ ደም ጠብታ የሚለፉ ነበሩ።

መላው ዓለም የፈረንሳይን ቀላል ድል ይጠብቅ ነበር። ነገር ግን የእግር ኳስ ነውና እንደታሰበው አልሆነም። ጨዋታው ተጀምሮ ሴኔጋል ያለምንም ፍርሃትና በከፍተኛ በራስ መተማመን መጫወቷን ቀጠለች።
በተለይም ልዩ ችሎታ ያለው ወጣቱ ኤል ሃጂ ዲዩፍ የፈረንሳይን ተከላካዮች ያስጨንቅ ነበር። በ30ኛው ደቂቃ ላይ ኤል ሃጂ ዲዩፍ በግራ መስመር የፈረንሳይን ተከላካይ ኢማኑኤል ፔቲትን አታልሎ ካለፈ በኋላ፣ ማራኪ ኳስ ወደ መሃል ላከ።
ፓፓ ባውባ ዲዮፕም በፈረንሳዩ ግብ ጠባቂ ፋቢያን ባርቴዝ ላይ ኳሷን ከመረብ አገናኛት! ሴኔጋል 1፣ ፈረንሳይ 0! ከጎሉ በኋላ የተደረገው ደስታና ዳንስ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ እጅግ ውብና ማራኪ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው።
ፓፓ ዲዮፕ ማሊያውን አውልቆ መሬት ላይ ሲያስቀምጥ፣ ሁሉም የሴኔጋል ተጫዋቾች በማሊያው ዙሪያ ተሰብስበው የአፍሪካን ባህላዊ ዳንስ በመደነስ ለዓለም አሳዩ።
ፈረንሳይ ያንን ግብ ለመመለስ እስከ መጨረሻው ብትሞክርም፣ የሴኔጋልን ጠንካራ ተከላካይና ግብ ጠባቂያቸውን ቶኒ ሲልቫን ማለፍ አልቻለችም።
በመጨረሻም ጨዋታው በሴኔጋል 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ። ይህ አሸናፊነት ዓለምን ያነጋገረ ተአምር ነበር። የዓለም ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ በዚያ ውድድር ላይ አንዲትም ግብ ሳታስቆጥር እጇን ሰጠች፤ ከምድቧም ሳታልፍ ቀረች።
ሴኔጋል ግን በዚህ ውድድር እስከ ሩብ ፍጻሜ በመጓዝ ዓለምን አኮራች። ዛሬ፡ ታሪክ ይደገማል?
በ2002 ዓ.ም በዚያች ቀን የአፍሪካ ህልም እውን ሆኖ ነበር። ያችን ታሪካዊ ግብ ያስቆጠረው ፓፓ ባውባ ዲዮፕ ዛሬ በህይወት የለም (በ2020 አርፏል)፤ ነገር ግን እሱ በዚያች ቀን በሴኡል የዘራው ጀግንነትና ወኔ ዛሬም በሴኔጋል አንበሶች ውስጥ ይንጸባረቃል።
ፈረንሳይ አሁንም ለሻምፒዮንነት ግምት ከሚሰጣቸው ሀገራት አንዷ ናት። በ2018 በሩሲያ ዋንጫ ያነሳች ሲሆን፣ በ2022 ደግሞ ለፍጻሜ ደርሳ በሚያስቆጭ ሁኔታ ዋንጫውን አጥታለች።
ዘንድሮ በዴምቤሌ፣ በምባፔ፣ በኦሊሴ እና በሌሎች ጠንካራ ተጫዋቾች ላይ ተስፋ ጥላለች። ሴኔጋል በበኩሏ የ2025 የአፍሪካ ዋንጫን በጨዋታ አሸንፋ በካፍ ውሳኔ አጥታለች። አሁንም ቢሆን ጠንካራ ቡድን ከገነቡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ዛሬ ምን ያሳዩን ይሆን?
ምሽት 4:00 ሰዓት በኒው ዮርክ ከተማ ተጠባቂው ጨዋታ ይደረጋል።
በተገኝ በፍቃዱ