AMN ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመላው ኢትዮጵያ በይፋ ባስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተለይ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሰባት አመታት ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል ዋንኛ መፍትሔ እየሆነ በሚገኘው በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በየዓመቱ በአማካይ 25 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያቸዉ ችግኝ ይተክላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በየአመቱ እያካሄደች ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ አልፎ የአረንጓዴነት ምጣኔን በመጨመር ወደ ውሃ አካላት የሚወርደውን የደለል መጠን እንዲቀንስ አስችሏል፡፡
መርኃ ግብሩ ከጎረቤት ሃገራት አልፎ የሌሎች አፍሪካ ሃገራትና የአለም አጀንዳና ተሞክሮ በመሆን ላይ የሚገኝ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያ በዚሁ አርአያነቷ የኮፕ-32 ጉባዔን ለማስተናገድ ተመርጣለች፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተለያዩ ዘርፎች እያስገኘ ካለው ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ጎን ለጎን ለተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ፣ ጉብኝቶችና ጉባዔዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የአፍሪካና የአለም መሪዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎችና ሌሎች ግለሰቦች ችግኝ እንዲተክሉና አሻራቸዉን እንዲያኖሩ በማድረግ ተሞክሮው አለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አለም አቀፍ ተቋማት፣ ዲፕሎማቶችና የዉጭ ሃገራት ዜጎች ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የአፍሪካና የአለም ሃገራት መሪዎችና ሌሎች ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የኢትዮጵያን አፈር በእጃቸዉ ነክተው አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸው እና የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ መሆናቸው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን በተግባር የሚያረጋገግጥ ነው፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ