AMN -ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

በአንድ ጊዜ ለ24 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል እጅግ ፈጣን እና ዘመናዊ የኃይል መሙያ ጣቢያ ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ ተመርቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያስገነባው ይህ ጣቢያ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማስፋፋት ለተያዘው ስትራቴጂ ትልቅ አቅም መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ40 በላይ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት በትጋት እየሰራ መሆኑ በምርቃቱ ላይ ጠቁመዋል።
ይህ የኃይል መሙያ መሰረተ ልማት ዝርጋታ በአዲስ አበባ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢና ወጪ ምርቶች የደም ስር በሆነው በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ላይ በደርሶ መልስ 16 የቻርጂንግ ስቴሽኖችን ለመገንባት የዲዛይን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቅሷል።
የትራስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሐሰን በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 2ሺ 230 ፈጣን የባትሪ መሙያ ስቴሽኖችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 1ሺ 176 ጣቢያዎች እንደ ሚያስፈልጉ ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ወደ 200 የሚጠጉት ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል::
በቴዎድሮስ ይሳ