የምንተክለዉ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ተስፋን፤ ልማትን፤ ምግባችንን እና ህልማችንን ነዉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የምንተክለዉ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ተስፋን፤ ልማትን፤ ምግባችንን እና ህልማችንን ነዉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምንተክለዉ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ተስፋን፤ ልማትን፤ ምግባችንን እና ህልማችንን ነዉ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል አካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ፤ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፤ አምባሳደሮች፤ የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አመራሮች፤ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፤ የሃይማኖት አባቶች፤ አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች: አባት አርበኞች፤ ባለሃብቶች፤ አርቲስቶች፤ አትሌቶች፤ ምሁራን ፤ የጤና ባለሙያዎች፤ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት ስምንት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከላቸዉን በመግለጽ ከዚህ ዉስጥ አዲስ አበባ ከ90 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን ተናግረዋል፡፡

በከተማ ደረጃ 90 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ትልቅ ትርጉም አለዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ መላዉ የመዲናዋን ነዋሪዎች በተቀናጀ መንገድ በማሳተፍ በተሰራዉ ስራም በ2010 ዓ.ም 2.8 እጅ ላይ ነበረዉን የመዲናዋ የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 24 እጅ ማሳደግ መቻሉንና መዲናዋም ለመኖር ምቹ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሃገር አቀፍ ደረጃ 8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር በይፋ መጀመሩን በመግለጽ፤ አዲስ አበባ 6 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ሽፋንዋን ወደ 30 እጅ የማሳደግ እቅዷን የበለጠ ከፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

የምንተክለዉ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ተስፋን ፤ ልማትን፤ ምግባችንን ፤ጥላችንን ፤ ልምላሜን እና ህልማችንን ነዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀሪ ግቦቻችንን ለማሳካት ተባብረን አሻራችንን እናኑር ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review