በከተማችን 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በበሻሌ ወንዝ ዳርቻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂደናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በከተማችን 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በበሻሌ ወንዝ ዳርቻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂደናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንኳን ለ2018 ዓ.ም የጋራ አሻራ ማኖር አደረሳችሁ !! ተስፋን እንትከል! በሚል መሪ ቃል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት በጋራ ሆነን የአረንጓዴ አሻራን በማኖር ስራችን ሀገራችን ዘመን የማይሽረው ታሪክ አስቀምጣለች ብለዋል፡፡

ባለፉ ሰባት ዓመታት እንደሀገር በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር 48 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪካዊ እና አስደማሚ አሻራ አኑረናል። በከተማችንም ባለፋት ሰባት ዓመታት 90 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ሽፋናችንን እጅግ ዝቅተኛ ከነበረበት 2 .8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማድረስ ችለናል ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብራችን የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ የነጠፉ ወንዞች እና አካባቢዎች ማንሰራራት ችለዋል። አዲስ አበባችንም ንፁህ፣ ውብ፣ ለመኖር ምቹ እና የቱሪስት ማዕከል መሆን ችላለች።

የምንተክለው ተስፋን፣ ልማትን፣ ልምላሜን፣ ጥላን፣ ምግባችንን ብሎም ብልፅግናን ነው። የምንተክለዉ ለዛሬ ጥቅማችን ብቻ ሳይሆን ለትውልድ እዳን ሳይሆን የልምላሜና የብልፅግና ምንዳን ለማውረስ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ በከተማችን 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት በበሻሌ ወንዝ ዳርቻ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂደናል ብለዋል፡፡

ውድ የከተማችን ነዋሪዎች በወንዝ ዳርቻዎች፤ በጤና፣ ትምህርትና በሃይማኖት ተቋማት፤ በግል ሴክተሮች እና በጎዳናዎች ለምግብነት የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን፣ የጥላ እና የውበት ዛፎችን በመትከል ከተማችን ውብ፣ ጽዱ ኢረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ከተማ ለማድረግ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህፃን አዋቂ ሳንል ሁሉም ዜጋ በጋራ በመሆን እንድናሳካው ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

ችግኝ መትከል ብቻ በቂ አይደለም እንክብካቤን ይፈልጋል ። ስለሆነም የተከልናቸውን ችግኞች መከታተል፤ መንከባከብ ይኖርብናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review