AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

ከራስ አልፎ ለትውልድ የሚተርፍ፣ ታሪክንና ተፈጥሮን የሚቀይር ተግባር ላይ መሳተፍ፤ ነገሩን በቅጡ ለተረዳ ሰው እጅግ ስሜትን የሚቀሰቅስ ታላቅ የጀግንነት ሥራ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ስምንተኛው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ግርማ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሥራውን ውጤት ወዲያውኑ በዓይኑ ለሚያይበት ነገር ትኩረት የመስጠት አዝማሚያ አለው ብለዋል።
ተግባርና ውጤት ሲቀራረቡ፣ አእምሯችን ምቾት ይሰማዋል ያሉት ቢሮ ኃፊው፣ ይህ በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ የሚመላለስ የትርፍና ኪሳራ ስሌት አመላካች በመሆኑ የሚመጣ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን፣ ዛሬ እኛ የምናከናውነው የአረንጓዴ አሻራ ተግባር የአእምሮ ሳይሆን፣ የልብ ሥራ ነው፤ ይሄ ለዛሬ ፈጣን ትርፍ የሚሰላ ሳይሆን፣ ለነገው ትውልድ፣ ለልጅ ልጆቻችን የሚተላለፍ የሕይወት ቅርስ ነው በማለትም ተናግረዋል።

እንደ መታደል ሆኖ፣ ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት የተጀመረው ይህ የልብ ሥራ፣ ዛሬ ደርሶ ልብን የሚያሞቅና በኩራት የምንመለከተው ታላቅ ውጤት እያሳየን ነው ሲሉም በንግግራቸው አስታውሰዋል።

ከተማችንን በልማት ዕቅዱ በተቀመጠው መሠረት 30 በመቶ በአረንጓዴ የመሸፈን ግብ በአጭር ጊዜ አሳክተን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባን ዘመናዊ፣ ውብና ስማርት (Smart City) የማድረግ ዕቅዳችንን በጽኑ መሠረት ላይ ይገኛልም ብለዋል።

ይህን ትልቅ ስኬት እውን ለማድረግ ወሳኝ ግብዓቶች ያስፈልጉን ነበር፤ እነርሱም፦ የመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና በፍጹም ምትክ የማይገኝለት የሕዝባችን ንቁ ተሳትፎ ናቸው ሲሉም አክለዋል።
ባለፉት አያሌ ዘመናት ስለ ችግኝ ተከላ በብዙ ተወርቷል፣ በብዙ ተጽፏል፤ ነገር ግን የሚጨበጥ ውጤት ያልተገኘበት ምክንያት እነዚህ ሁለት ወሳኝ ግብዓቶች ተቀናጅተው ባለመኖራቸው ነበር በማለትም ጠቅሰዋል።
ዛሬ ግን ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን እውቅና መስጠትና ይህ በጎ ጅምር እንዲቀጥል መመኘት ይኖርብናል ስሉ መናገራቸውን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።