AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 23 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የግል እጩ መቀመጫ ማግኘታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው ሊባል ይችላል።
ይህ ክስተት በከተማዋም ሆነ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ እና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ሰፊ አንድምታ እና አስተዋጽኦ አለው።
ከዚህ ቀደም በነበሩት የምክር ቤት ስብስቦች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ መቀመጫዎቹ በአንድ ገዥ ፓርቲ ወይም በጥቂት ፓርቲዎች ብቻ የሚወሰዱ ነበሩ።

ይህን ያክል ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ፓርቲዎች መግባታቸው፣ ሥርዓቱ ከ”አንድ ፓርቲ የበላይነት” ወደ እውነተኛ “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት” እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል።
በተለያዩ ጊዜያት ምሁራን እንደሚያነሱት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምክር ቤት መቀመጫ ማግኘታቸው፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጠው የፖለቲካ ምህዳር በተግባር መሻሻል ማሳየቱን እና የሕዝብ ድምፅ በተለያዩ የፖለቲካ አማራጮች በኩል ውክልና ማግኘቱን ያረጋግጣል።
አዲስ አበባ የተለያየ ፍላጎት፣ ፍልስፍና እና ፍላጎት ያላቸው ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት ስትራቴጂካዊ ከተማ ናት።

23 ፓርቲዎች እና የግል እጩው ምክር ቤት መግባታቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ልዩ ልዩ ፍላጎቶች፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ወደ ምክር ቤቱ መድረክ ለማምጣት ያስችላል።
ሕዝቡ የመረጣቸው አካላት በመሆናቸው፣ በሕግ አውጪው አካል ውስጥ ማንኛውም ድምፅ ሳይገለል እንዲሰማ እና የፖለቲካ አካታችነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
የጠንካራ ዴሞክራሲ መገለጫው አስፈጻሚውን አካል የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ጠንካራ የሕግ አውጪ አካል መኖሩ ነው።
የአንድ ወገን ውሳኔዎችን እና አዋጆችን ያለምንም ጥያቄ የማጽደቅ ልማድን ያስቀራል።
የተለየ ሐሳብ ያላቸው በርካታ ተፎካካሪዎች መኖራቸው ማንኛውም በከተማዋ ላይ የሚወጣ ፖሊሲ፣ በጀት ወይም ሕግ በጥልቀት እንዲመረመር፣ እንዲከራከርበት እና እንዲፈተሽ ያደርጋል።
ይህ ደግሞ ለአስተዳደራዊ ግልጽነት እና ለቅንነት መረጋገጥ ዋስትና ነው።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ማዕከል በመሆኗ በከተማዋ ምክር ቤት ውስጥ የሚታየው ለውጥ ለሌሎች ክልሎችም አርአያነት አለው።
በጠመንጃ ወይም በኃይል ሳይሆን በምርጫ ካርድ እና በሰላማዊ መንገድ ሥልጣንን የመጋራት እና በሃሳብ የመሸናነፍ ባህልን ያዳብራል።
ዜጎች በምርጫ ሥርዓቱ እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት ከመጨመሩም ባሻገር ድምፃቸው ዋጋ እንዳለውና ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በተግባር እንዲያዩ ያደርጋል።
በአጭሩ ይሄንን ያክል ቁጥር ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክር ቤት መግባቱ፣ በሀሳብ ብዝሃነት የታነጸ፣ የሰለጠነ ፖለቲካን የሚያበረታታ እና ከተማዋን በጋራ ስምምነት ለመምራት የሚያግዝ ታሪካዊ እርምጃ ሲሆን፣ ለወደፊት የዴሞክራሲ ጉዞም ጠንካራ መሠረት የሚጥል ክስተት ነው።
በታምራት ቢሻው