AMN- ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

የፓኪስታን ዜግነት ያላቸው ዝሻን ካሊድ፣ ፍርዝ መሃመድ እና መሀመድ ጀናይድ የተባሉ ተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ሰኔ 4 እና ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጎሮ አትሌቶች መንደር እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተከራዩት የመኖሪያ ቤት ውስጥ የህንድና የባንግላዴሽ ዜግነት ያላቸውን ግለሰቦች በመያዣነት በመጠቀም የግል ተበዳዮችን በገመድ በማሰርና በፕላስተር በማፈን ከ15 እስከ 30 ሚሊየን ብር በመጠየቅ ጥቃት አድርሰውባቸዋል ብሏል ፖሊስ።

ተጠርጣሪዎቹ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ሰኔ 11ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የገቡ 4 የህንድ ዜጎችን በማሰርና በመደብደብ ከ15 እስከ 25 ሺህ የህንድ ሩፒ አስልኩ በማለት ድብደባ ሲፈጽሙባቸው እንደነበር የግል ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል ሲል ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

የወንጀሉ መፈጸም መረጃ የደረሠው የለሚ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ተገቢውን የፍርድ ቤት መያዣና የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት ባከናወነው ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዎቹን ለወንጀል ድርጊት ሲጠቀሙበት ከነበረው ቢላዋ፣ ገመድና ፕላስተር እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘቦች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠርጣሪዎቹ እንዲያዙ መረጃ በመስጠት ላደረጉት ቀና ትብብር ምስጋናውን ያቀረበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙም ለፖሊስ መረጃ መስጠት እንደሚገባም መልዕክት ማስተላፉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡