AMN- ሰኔ 19/2018 ዓ.ም
በማንኛውም ቤተሰብ ፣ ማህበራዊ ህይወት፣ ተቋም ወይም የስራ ግንኙነት ውስጥ አለመስማማቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ አለመግባባቶች በንግግርና በሰለጠነ መንገድ የማይፈቱ ከሆነ ጥርጣሬን ከመፍጠራቸውም በላይ ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ፡፡
የመነጋገር ባህል ሲኖር ችግሮችን በኃይል ወይም በጦርነት ከመፍታት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት ያስችላል። ይህም የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ከጥፋት ይታደጋል።
በቤተሰብ ፣ በማህበረሰብ ፣ በተቋምም ሆነ በሃገር ደረጃ ጠንካራ የመነጋገር ባህልን መገንባት መከባበርንና አንድነትን ለማጠናከር ፣ የተሻሉ ውሳኔዎችን ለመወሰን ፣ እውቀትንና ግንዛቤን ለማስፋትና ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ለመገንባት ያግዛል፡፡
ሰዎች በውስጣቸው ያለውን ሀሳብ ፣ ፍላጎት እና ስሜት በግልጽ እንዲነጋገሩ ፣ የሀሳብ ልዩነቶችን እንዲያጠቡ እና አንዱ ሌላውን በደንብ እንዲረዳ ከማድረግ ረገድ ንግግር ያለው ሚና የላቀ ነው፡፡
የመነጋገር ባህል አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት መድረክ ሳይሆን ፣ ሁለቱም ወገኖች ተደምጠው በጋራ የሚያተርፉበት የጥበብ አውድማ ነው።
አንድ ሰው ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ ወይም ከትዳር አጋሩ ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክረው በመነጋገር ሲሆን ፣ ይህም የልብን ለማውጋት፣ ደስታንና ሀዘንን ለመጋራትና መተማመንን ለማሳደግ ያግዛል፡፡
አዳዲስ ነገሮችን ለመማር፣ መረጃዎችን ለመቀበልና ለማስተላለፍ መነጋገር ዋንኛው መንገድ ነው፡፡ በስራ ቦታም ሆነ በትምህርት አለም ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ውጤታማ የተግባቦት ክህሎት ያስፈልጋል።
ጭንቀትን ፣ ፍርሃትን ወይም ከባድ ስሜትን አምቆ መያዝ አእምሮአዊና አካላዊ የጤና እክሎችን የሚፈጥር ሲሆን በግልጽ መነጋገር ግን የአእምሮ እረፍትና መረጋጋትን ይፈጥራል፡፡
መነጋገር ይህንን እና መሰል ጠቀሜታችን ካሉት መነጋገር የማይፈልጉት ሰዎች እነማን ናቸው? ለመነጋገርስ ፈቃደኛ የማይሆኑበት ምክንያት ምንድነው የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱ የስነ-ልቦናና የባህሪ ችግር ያለባቸው ሰዎች በአብዛኛው ለመነጋገር ቁርጠኛ አይደሉም፡፡ በአንድ ጉዳይ በጣም የተከፉ፤ የተበሳጩና የተቆጡ ሰዎች ፣ በግል ሕይወታቸው እና በማኅበራዊ ግንኙነታቸው አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ቁርጠኛ ያልሆኑ ሰዎች መነጋገርን አይመርጡም፡፡
ከሰዎች ጋር መገናኘትና ማውራት ከፍተኛ ጭንቀት የሚፈጥርባቸው ግለሰቦች ፣ በከባድ ሐዘን ወይም በድብርት ውስጥ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከማንም ጋር የመነጋገር ፍላጎትና አቅም ሊያጡ ይችላሉ።

በማንኛውም ግንኙነት ውስጥ ውጤታማ እና ጤናማ መግባባትን ለመፍጠር የራስን ምላሽ ብቻ ከመመመለስ ይልቅ የሌላኛውን ወገን ስሜት በትክክል መረዳትና ማዳመጥ ፣ የራስን ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ከመደምደም መቆጠብ፣ የሌላውን ሰው እይታ እና ልዩነት ለመቀበል ወይም ለመረዳት ፈቃደኛ መሆን ጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በጨዋነት እና በግልጽነት የሚሰማንን እና የምናስበውን ነገር ሳንደብቅ መናገር ፣ ስሜትን መቆጣጠር ፣ በንዴት ወይም በስሜት መጋለብ ውስጥ ሆኖ ውሳኔ ከመስጠት ወይም ከመናገር መቆጠብ ፍሬያማ ተግባቦትን ለመፍጠር ያግዛል፡፡
አንዳንድ ሰዎች የሌላኛውን ሰው ሃሳብ በአግባቡ ሳይረዱና ሳይገነዘቡ ለመውቀስ ፣ ለመፈረጅና ለመፍረድ ይሞክራሉ፡፡
ይህም ጤናማ ተግባቦት እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ይበልጥ እንዲወሳሰቡ ያደርጋሉ፡፡
ከሁሉም በላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና ለመመካከር የተቀመጡ ሰዎች እርስ በርስ የሚከባበሩ ከሆነ ለመግባባት የሚያስቸግራቸው አንዳችም ችግር አይኖርም፡፡
እርስዎስ የመነጋገርን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዴት ተመለከቱት? ሃሳብዎን ያጋሩን !
በወንድማገኝ አሰፋ