ምክር ቤቱ ሦስት አዋጆችን አፀደቀ

You are currently viewing ምክር ቤቱ ሦስት አዋጆችን አፀደቀ

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስና የኢትዮጵያ ካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ ከአዋጅ ማፅደቅ በተጨማሪ የፌዴራል መንግስት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት እቅድ ላይ በዝርዝር ተወያይቷል።

የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ ረቂቅ አዋጆቹን የተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ሰብሳቢው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በታክስ ከፋዩና በታክስ ሰብሳቢው የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ተጠያቂነትና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ብሎም ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ የዕድገት ጉዞና የለውጥ ፕሮግራሞች እንዲሁም የፖሊስ አወጣጡን በመረጃ ላይ የተደገፈ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ዘመናዊ ጠንካራና ህጋዊ መሰረት ያለውና ዓለም አቀፍ ስርዓትን የተከተለ የስታቲስቲክስ ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የኢትዮጵያ ካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ እያደገ የመጣውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሻገር፣ የአረንጓዴ ኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦችን በመመርመር ሦስቱን ረቂቅ አዋጆች መጽደቃቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review