AMN-ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው አዲስ ስኬት እና ታሪካዊ ቅርሶቿን ወደ ሀገር የመመለስ ሂደት የዘርፉን ትንሳኤ እያበሰረ ይገኛል።
መንግስት ለቱሪዝም ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች ከማዘመን ባለፈ፣ ለዘመናት በባዕድ ሀገራት እጅ የቆዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ወደ እናት ሃገር እንዲመለሱ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተከናውነዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የተሳኩ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በተለይም ከእንግሊዝ እና ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ውድ የሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት ፣ የነገሥታት አልባሳትና የጦር መሣሪያዎች ወደ እናት ሀገራቸው እንዲመለሱ አስችለዋል።

ይህ የታሪክ ማስተካከያ እርምጃ የኢትዮጵያን ኩራትና ማንነት ከመመለሱም በላይ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም መስህብነቷን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ከአምስቱ ዋና ዋና ዘርፎች ውስጥ በማካተት የላቀ ትኩረትን እንዲያገኝ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለፃቸው ይታወሳል።
ከቅርሶች መመለስ ጎን ለጎን ፣ ዘርፉን ለማነቃቃት የተሰጠው ትኩረት በከፍተኛ መሠረተ ልማት ግንባታ የታገዘ ነው።
እንደ አንድነት፣ እንጦጦ፣ ወንጪ እና ጎርጎራ ያሉ ግዙፍ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው የሀገሪቱን የቱሪዝም አማራጮች አብዝተዋል።

እነዚህ ዘመናዊ መዳረሻዎች ታሪካዊ ቅርሶቿን ከዘመናዊ መዝናኛዎች ጋር በማቀናጀት አዲስ የቱሪዝም ገጽታ የፈጠሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻነት ስሟ በግንባር ቀደምትነት እንዲነሳና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱም ይገኛሉ።
በሚካኤል ህሩይ