አዲስ አበባ ውስጥ አራት ሞሎች በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ አበባ ውስጥ አራት ሞሎች በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

ለጎብኚዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፋት አዲስ አበባ ውስጥ በርከት ያሉ ሞሎች እየተገነቡ እንዳሉና አራት ሞሎች በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍን አስመልክቶ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣ ቱሪዝም ኢኮኖሚ የሚሆነው በዘርፉ ግብይት ሲፈጠር ነው ብለዋል፡፡

በቱሪዝም መዳረሻዎች አካባቢ ለቱሪስቶች የሚሆን ምግብ፣ ቡና፣ ቅርጻቅርፆች፣ አልባሳት እንዲሁም ሱቆች መኖር እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

ጎብኝዎች መጥተው የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን አይተው መሄዳቸው ብቻውን ቱሪዝምን ስለማያነቃቃ አንድ ጎብኚ ልቡ ተደስቶ፣ ተዝናንቶ ይዞ የመጣውን ወጪም አውጥቶ መሄድ አለበት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የሞሎችና የሱቆች ግንባታ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ አዲስ አበባ ላይ በርከት ያሉ ሞሎች እየተገነቡ ስለመሆኑ በማንሳት ሶስት አራት የሚጠጉ ሞሎች በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ሞሎች በጥራት ደረጃ በዓለም ጥሩ የሚባሉ መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህ ስራ ሲጀምሩም ሞል አልባ ከነበረው በመነሳት አፍሪካ ውስጥ የተሻለ ሞል ካላቸው ሃገራት ተርታ ያስገባናል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ትላልቅ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃ ሲሆን ይሄም የዜጎች፣ የግል ዘርፉ እንዲሁም የብዙ ሰዎች የሃብት እና የዕውቀት ድምር ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review