ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝምና ከውጭ ጎብኚዎች ከአምስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

You are currently viewing ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝምና ከውጭ ጎብኚዎች ከአምስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

AMN ሰኔ 23/2018

ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝምና ከውጭ ጎብኚዎች ከአምስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 204 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን አስተናግዳለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል ርዕስ የቱሪዝም ዘርፉን በተመለከተ ከኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት ኢንቨስት የተደረገበት የቱሪዝም ዘርፍ ልክ እንደ ግብርናውና ኢንዱስትሪው ሁሉ ከፍተኛ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ100 ሺህ፣ ከ2016 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር ደግሞ ከ300 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።

ከዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ከውጭ የቱሪስት ፍሰት (ማይስ) በአጠቃላይ ከአምስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱ የሚያሳየው ቱሪዝም ውጤት እያመጣ መሆኑን ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘንድሮ ከ50 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ተንቀሳቅሰው የተለያዩ መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ከአምናው የአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን፣ ከታች አምናው ደግሞ የዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮን ጎብኚዎች ብልጫ አለው ነው ያሉት።

በዚህም 79 ቢሊየን ብር ገቢ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዘንድሮ 204 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ይህም ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው በ166፣ ከአምናው በ50 ጉባኤዎች ብልጫ አለው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ በዚህ ዓመት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች 166 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸውን ነው ያነሱት።

በዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት እየመጣ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ኮንፈረንስ ማድረግና በቡድን መጎብኘት እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review