ታሪካዊ ማንነቷን ጠብቃና አዘምና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ

AMN – ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መቀመጫነቷ ባለፈ ታሪካዊ ማንነቷን ጠብቃና አዘምና ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች፡፡

መንግሥት ታሪክን የማደስ፣ የመጠበቅና ለትውልድ የማሻገር ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በከተማዋ የታደሱ ቅርሶች እና የተገነቡ ግዙፍ የቱሪስት መስህቦች በተግባር አረጋግጧል።

ለአብነትም በመሃል ፒያሳ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን የጀግነነት ታሪክ የሚዘክር የቱሪስት መስህብ ሲሆን፣ ይህ ማዕከል የጀግኖች አባቶችና እናቶችን ታሪክ በክብር የሰነደ፣ የጦር መሪዎችን ሐውልትና ቅርሶች የያዘ ነው፡፡

የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከ2 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዓለም አቀፍ የፓን አፍሪካን አዳራሽ በማካተቱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

በተጨማሪም የአንድነት ፓርክ የነገሥታትን ታሪክ ከተፈጥሮ ብዝሃነት ጋር ያጣመረ ሲሆን፣ በከፍተኛ ጥራት የታደሰው የብሔራዊ ቤተ መንግሥትም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች መዳረሻ ሆኗል፡፡

ከታሪካዊ ቅርሶች ባለፈ በቅርብ ዓመታት የተገነቡት የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ዘመናዊ ፓርኮች የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል።

በተለይም ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ድረስ የሚዘልቀው የ56 ኪሎ ሜትር ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ውብ እና ከብክለት ነፃ ከማድረግ ባለፈ፣ ቀደም ሲል ለጎርፍ አደጋ ስጋት የነበሩትን አካባቢዎች ለሽርሽር ምቹና ደኅንነታቸው የተጠበቀ የመዝናኛ ስፍራዎች አድርገዋል።

እንዲሁም ሰፊ የመኪና፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የንግድና ማራኪ የገበያ ማዕከላትን አቀናጅተው በመያዛቸውም ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራና የኢኮኖሚ ዕድል ፈጥረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማዋ በተተገበሩ ግዙፍ የልማት ሥራዎች፣ አዲስ አበባ በጥንታዊ ታሪኳ እና በዘመናዊ የከተማ ልማቷ የተዋበች፣ ሳቢ እና ለቱሪስቶች ተመራጭ መሆኗን በተለያዩ ጊዜያት መዲናዋን የጎበኙ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች አረጋግጠዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review