የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ገለጸ

AMN- ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የአፈፃፀም መለኪያዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዋልታነቱን በድጋሚ አረጋግጧል ሲሉ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታውቀዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ይህንን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባንኩ የገበያ ድርሻውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉንና አዳዲስ የታሪክ አሻራዎችን ማስመዝገቡን አብስረዋል።

ትናንት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ707.4 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ታላቅ ስኬት ያስመዘገበ ሲሆን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ ከ2.4 ትሪልዮን ብር በላይ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የባንኮች ታሪክ ይህን ያህል ተቀማጭ ገንዘብ በአንድ ዓመት ውስጥ ሲሰበሰብ በታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ከ6 ዓመት በፊት ከነበረው በ4 እጥፍ ማደጉን አመልክተዋል።

ባንኩ ባለፈው በጀትዓመት ከ648.02 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ ከ90.7 በመቶ በላይ (588.11 ቢሊዮን ብር) የሚሆነው ብድር ለግሉ ዘርፍ መሰጠቱን ገልፀዋል።

በ2019/20 በጀት ዓመት ባንኩ ከሰጠው ብድር ለግሉ ዘርፍ የተሰጠው 10 በመቶ አካባቢ እንደነበር ገልፀው፣ የዘንድሮው አፈፃፀም ባንኩ ለግሉ ዘርፍ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

በባንኩ የተሰጠ ጠቅላላ የብድር መጠን 1.64 ትርሊዮን ብር መድረሱንም ነው አቶ አቤ የገለፁት።

በብድር አሰባሰብም ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ 546.26 ቢሊዮን ብር ብድር መሰብሰቡን አመልክተዋል።

የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከ1.4 በመቶ በታች እንደነበር ገልፀው፣ ይህም ባንካችን በብድር አሰባሰብ ዙሪያ እየሠራ ያለውን ውጤታማ ሥራ እንደሚያመለክት አስረድተዋል።

በውጭ ምንዛሬ ግኝትም በተመሳሳይ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት አቶ አቤ፣ በዓመቱ ከ5.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በዲጂታል ክፍያ ዘርፍም ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበ የገለፁት አቶ አቤ፣ በዓመቱ በ3.48 ቢሊዮን የገንዘብ ዝውውሮች ከ22.24 ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በባንኩ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች መንቀሳቀሱን አስረድተዋል።

የዲጂታል የክፍያ አፈፃፀም በሀገር ደረጃ 70 በመቶ ድርሻ እንዳለው እና ይህም በዲጂታል ክፍያ ዘርፍ ባንኩ የሀገሪቱ ዋልታ መሆኑን ያስመሰከረበት እንደሆነ አቶ አቤ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሀገር መልክ ነፀብራቅ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ አስቻይ የኢኮኖሚ ሥርዓት በሀገራቱ መዘርጋቱ ለተመዘገበው ውጤት ምክንያት በመሆኑ ይህን ላደረገው መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

በገበያው ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ የላቀውን ድርሻ ለመውሰድ ትልቅ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ የገለፁት አቶ አቤ፣ ለመላው የባንኩ ሠራተኞች ትጋት እና ቁርጠኝነት እንዲሁም ለንደንበኞች ላቅ ያለ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ባንኩ የላከው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review