በግብርናው ዘርፍ የታየው እድገት በድርቅ እና ረሃብ ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN—ሀምሌ 1/2018 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገሪቱን የግብርና ምርታማነትና የኢኮኖሚ ብዝሃነት ስኬቶችን አብራርተዋል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ከሚኖር ጥገኝነት በማውጣት ዘርፈ-ብዙ ለማድረግ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

በዚህም ዘንድሮ በ29 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የዘርፉን የምርታማነት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ አስደናቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ከዚህስ ቀደም የውጭ ኤክስፖርት ልምድ ባልነበረው የአቮካዶ ምርት፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ኤክስፖርተር በመሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት መጀመሯ የዚሁ ስኬት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ በግብርናው ዘርፍ የታየው አዲስ የእድገት ምዕራፍ ቀደም ሲል በድርቅ እና በረሃብ ይታወቁ የነበሩትን እንደ ቦረና፣ ሶማሌ እና አፋር ያሉ አካባቢዎችንም ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረ ይገኛል።

እነዚህ ቀጠናዎች በአሁኑ ወቅት ሰፊ የግብርና እርሻዎች የሚታዩባቸው እና ውጤታማነታቸው በተግባር የተረጋገጠ ቀዳሚ አካባቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእነዚህ አበረታች አመላካቾች መነሻነትም የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ዕድገት ይፋ የሚሆነው በመስከረም ወር ቢሆንም የግብርናው ዘርፍ ብቻ በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review