ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የታየ ጽናት

You are currently viewing ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የታየ ጽናት

AMN- ግንቦት 25 /2018 ዓ/ም

ግንቦት 24 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ መጽሐፍ ወሳኝ ምዕራፍ ሆኖ ተክትቧል፡፡ በዚች ቀን ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ መሻታቸውን ለዓለም አሳይተዋል፡፡ በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ የታየው የሕዝብ ማዕበል ኢትዮጵያን ለማጽናት ያለውን ብርቱ ፍላጎት ያንጸባርቃል፡፡

ሚሊዮኖች ድምጻቸውን ለመስጠት ከሌሊት እስከ ሌሊት ተሰልፈው ለጫናዎች ባለመበገር በምርጫ ሂደት ላይ ያላቸውን እምነትና የባለቤትነት ስሜት አሳይተዋል።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ሥርዓት ባለው መንገድ መጠናቀቁ የዜጎችን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ብስለት ያሳየ ክስተት ነው ፡፡

በግርግር ስልጣን ለመቆናጠጥ ያሰፈሰፉ ኃይሎች የሚነዙት አሉባልታ ድምፅ ከመሰጠት አላደናቀፋቸውም ፣ ይልቅ ከአድማስ አድማስ የሚያስተጋባ መልዕክት አስተላልፈዋል – ኢትዮጵያ ትመርጣለች ፤ልጣን በምርጫ ብቻ ! የሚል፡፡

ይህ ታላቅ መልዕክት ለነውጥ ያሰፈሰፉትን ቅስም ሲሰብር ፣ የኢትዮጵያን ሃገረ መንግስት መጽናት ለሚሹትና ለሚተጉት ብርታትን እንዲሰንቁ አስችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የስልጣን ምንጭ በህዝብ ይሁንታ በምርጫ ብቻ የሚገኝ መሆኑን ኢትዮጵያውያን በትናንትናው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሳዩት ጽናት አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝቡ ተሳትፎ እጅጉን በመደነቅ ፣ “ከፈጣሪ በቀር ሕዝባችንን አሟልቶ ሊያውቅ እና ሊገመግም የሚችል ማን ነው?” ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሚገጥሙት ተግዳሮቶች የሚሰጠውን በሳል ምላሽ እና ሐገርን የማጽናት ጥበብ የሚያመልክት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት ምርጫዋን አሳውቃለች፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለበት ፣ የስልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን ፣ ሐገር በሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት ማጽናት እንደሚገባ በአደባባይ ፍላጎቷን አሳይታለች፡፡

ይህም መጻኢ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያደርግ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ተመራጮች ያከበራችሁን አክብራችሁ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ዋጋ የከፈለውን ይሄንን ሕዝብ በንጽሕና ለማገልገል ያብቃችሁ።” ሲሉ ያስተላለፉት የአደራ መልዕክት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው ኃላፊነት ታላቅ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review