በአዲስ መሶብ ማዕከላት ከ262 ሺህ 784 ለሚበልጡ ተገልጋዮች አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮች እርካታን ማሳደግ ተችሏል

You are currently viewing በአዲስ መሶብ ማዕከላት ከ262 ሺህ 784 ለሚበልጡ ተገልጋዮች አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮች እርካታን ማሳደግ ተችሏል

AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‘አዲስ መሶብ’ ዲጂታል ማዕከላት 99 በመቶ የተገልጋይ እርካታ ማስመዝገባቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ የአስተዳደራቸውን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማዋን ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በተደረገው መጠነ ሰፊ ሪፎርም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጨባጭ እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ እየተመዘገበ ነው።

ከተማ አስተዳደሩ አገልግሎቶችን ለማዘመን በሰጠው ልዩ ትኩረት፤ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ 11 አዳዲስ “አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ማዕከላት ተከፍተው ወደ ስራ ገብተዋል።

ማዕከላቱ እስካሁን ከ 262 ሺህ 784 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች አገልግሎት ሰጥተዋል። አገልግሎቱን ያገኙ ነዋሪዎች እርካታ 99 በመቶ መድረሱን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።

እንዲሁም 150 የሚሆኑ አገልግሎቶች በማዕከላቱ በአንድ ጣሪያ ስር እየተሰጡ ሲሆን ከ8 ተቋማት የተለዩ 41 አገልግሎቶች ህዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮች በተንቀሳቃሽ የአዲስ መሶብ መኪኖች በመዘዋወር እየተሰጡ ነው ብለዋል።

በተጨማሪ ወደ ማእከሉ ያልገቡ ተጨማሪ 45 አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በመደረጋቸው፣ በአጠቃላይ በከተማዋ በዲጂታል የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶች ብዛት 392 መድረሱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አገልግሎት በሚበዛባቸው ከ19 በላይ ተቋማት ላይ የተደረገው ሪፎርም ስራና ሰራተኛን በሚገባ ማገናኘት መቻሉን አመላክተዋል።

በየሳምንቱ መጀመሪያ በተለያዩ ተቋማት በሚካሄደው በ’ወርቃማው ሰኞ’ ሰራተኛው እና አመራሩ ስለተቋሙ ተልዕኮ የሚወያዩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ተፈጥሯል ብለዋል።

እንዲሁም በባለጉዳይ ቀናት ረቡዕ እና አርብ ፤ ከወረዳ እስከ ማዕከል ያሉ የተቋማት ኃላፊዎች በቢሮ ተገኝተው ተገልጋዮችን ማስተናገድ እና ችግሮችን መፍታት ተችሏል ነው ያሉት።

በእነዚህ የባለጉዳይ ቀናት ላይ በተደረገ ምልከታ፤ በአማካይ 90በመቶ የሚሆኑት አመራሮችና ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ በመገኘት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ አገልግሎት ከጠየቁ ተገልጋዮች ውስጥ 87 በመቶ የሚሆኑት በአግባቡ አገልግሎት ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 13 በመቴ ተገልጋዮች በአግባቡ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review