AMN- ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሀብት ፍሰትና የልማት መነቃቃት እያስተናገደች እንደምትገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ ለምክር ቤት ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለጹት ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት በርካታ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለ22 ሺህ190 ኢንቨስተሮች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱንና ነባር ሥራዎቻቸውን ለሚያሰፉ 1ሺህ 632 ኢንቨስተሮች ደግሞ የማስፋፊያ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት ኢንቨስተሮች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባራዊ ሥራ የተሸጋገሩ ሲሆን፥ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በከተማዋ ኢኮኖሚ ውስጥ በማንቀሳቀስ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል ፡፡
በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እና አሳታፊ እንዲሆኑ ታስቦ ወደ ተግባር የገባው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮግራም እጅግ አስደናቂ ውጤት ማስመዘገቡንም ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡

በአጋርነት በተቀረጹ የተለያዩ የልማት ዘርፎችና ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ1.3 ትሪሊዮን ብር በላይ የካፒታል ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃና በፍጥነት ማሳደግ መቻሉን የተናገሩት ከንቲባዋ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጓት የሚችሉ ታላላቅ ልማቶች እውን እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡
በያለው ጌታነህ