የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር ውይይት በአዲስ አበባ ተከፈተ

You are currently viewing የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር ውይይት በአዲስ አበባ ተከፈተ

AMN ሐምሌ 14/ 2018 ዓ.ም

የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር (GASPI) የመጀመሪያው የአፍሪካ ቀጠናዊ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ ተከፈቷል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት (IFA)፣ ኦዲአይ ግሎባል አድቫይዘሪ እና ግራቪታስ ሶቨሬን እና ስትራቴጂክ አድቫይዘሪ በጋራ የተዘጋጀው ይህ ከፍተኛ ደረጃ ውይይት፣ እ.አ.አ በመጋቢት 2027 በአቢጃን ከሚካሄደው የGASPI ጉባኤ በፊት የተግባራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመለየት ያለመ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ፣ ስብሰባው እያደገ የመጣውን አጋርነት ለመገምገም እና ለ2027ቱ ጉባኤ ዝግጅት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) እና የባህረ ሰላጤ አገራት የኢኮኖሚ ልዩነት ስልቶች ለሁለቱም ወገኖች ታሪካዊ የትብብር እድል መፍጠራቸውን አጉልተዋል።

አምባሳደር ሃደራ አጋርነቱ ከባህላዊ የንግድ ልውውጥ ባለፈ ወደ መሠረተ ልማት፣ ታዳሽ ኃይል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የምግብ ዋስትና መሸጋገሩን ጠቅሰው፤ የአፈፃፀም ክፍተቶችን በጠንካራ ተቋማት እና ምቹ ፖሊሲዎች ማጥበብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ የአዲስ አበባ ስብሰባ ከአራቱ ቀጠናዊ ምክክሮች የመጀመሪያው ሲሆን፣ ቀጣዮቹ ስብሰባዎች በደቡብ አፍሪካ፣ በሞሮኮ እና በጋና እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

ውይይቱ በቁልፍ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶችን በማካሄድ እና ቀጣይነት ያለው የተቋማዊ ትብብር አስፈላጊነትን በማረጋገጥ መጠናቀቁን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review