AMN ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፣ የዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ሂደት እና ‘የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስ’ ኢኒሼቲቭ ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከስምምነት ላይ መደረሱን ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ስብሰባን አካሂዷል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በአመቱ ውስጥ እንዲፈፀሙ ያስቀመጣቸውን ተግባራት አፈፃፀም በጥልቀት በማየት አቅጣጫ አስቀምጧል።
የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የስራ ክንውን፣ የዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ሂደት እንዲሁም ‘የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስ’ ኢኒሼቲቭ ትግበራ አፈጻጸምን ገምግሞ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሀገራችን በመከናወን ላይ የሚገኙ አዳዲስ የዲጂታል ስራዎች ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጋር ያላቸውን ተጣጣሚነትን በውይይታችን ተመልክተናል ነዉ ያሉት፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችን በእመርታ የሚያድግበት ዘመን ላይ እንደመሆኑ፤ ምክር ቤቱም ለዚሁ ዕድገት ተገቢውን ሚና ለመወጣት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡