የተባበረ ህዝብ ሀገር መገንባት እንደሚችል ለዓለም ማሳያ እንሆናለን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የተባበረ ህዝብ ሀገር መገንባት እንደሚችል ለዓለም ማሳያ እንሆናለን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በህግ የበላይነት እና በትብብር ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሀገራዊ መሰረት እየጣለች መሆኑንና አጠቃላይ ሀገራዊ ጥረቷም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ክንድ 800 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል የሚያደርገውን ታሪካዊ ንቅናቄ በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው፣ ጥንካሬ ያለው ሀገራዊ ግንባታ የሚቻለው ህዝብ ተወያይቶ የጋራ፣ አሳታፊ እና አስተማማኝ የህግ መሰረት ሲጥል መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ መሠረቶች ሳይጣሉ የሚሰሩ ስራዎች በማንኛውም አጋጣሚ ፈራሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ አሁን እየተከናወኑ ያሉ የልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለነገዋ ኢትዮጵያ እና ለተተኪው ትውልድ ተስፋን የመትከል ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ዛሬ 800 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ከጥዋት ጀምረው እየተረባረቡ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ዛፍ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ምግብ፣ ጥላ፣ ውበት እንዲሁም የምትመናመነው ተፈጥሯችን ዘብ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በጀመሩት የተባበረ መንገድ በመቀጠል በዛሬው ዕለትም ሆነ በሚቀጥሉት ሳምንታት ችግኞችን በመትከል የተጣለውን ሀገራዊ ግብ እንዲያሳኩና ተስፋን መትከላቸውን እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review