AMN ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

የደቡብ ሱዳን ተወካይ ኮሚኒቲ እና ዲፕሎማቶች በጎሮ የወንዝ ዳርቻ ላይ አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል። በዕለቱ የተገኙት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አባላት የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅና ውበትን ለመጨመር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ይህ ተግባር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ትብብር በተግባር ያሳየ ሆኗል።

የኮሚኒቲውና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አባላት ችግኝ በመትከል ብቻ ሳያበቁ በቀጣይ የቦታውን አረንጓዴነት ለማረጋገጥ በበጋው ወራትም ወደ ስፍራው ተመልሰው የተከሏቸውን ችግኞች ውኃ በማጠጣትና በመንከባከብ ለውጤት ለማብቃት ቃል ገብተዋል።

በኤምባሲው ተወካይ በዶክተር ቴር የተመራው ይህ የልዑካን ቡድን በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ ቤተ-መጽሐፍት ለመገንባት ትልቅ ቃል ገብተዋል። ይህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩን ማህበራዊ ፋይዳ ይበልጥ ከፍ አድርጎታል።

ይህ የበጎ አድራጎትና የልማት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ታሪካዊ ወዳጅነት ምን ያህል በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠ ነው። በመርሃ ግብሩ ላይ የኢንተርናሽናል ሊበርቲ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሮፌሰር አብርሃም ነጋ የተገኙ ሲሆን መርሃ-ግብሩ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት ይበልጥ የሚያደምቅ ነዉ።