AMN – ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

የህይወትና ንብረት ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ ተቋማት የደህንነት መስፈርቶችን ሊያሟሉ እንደሚገባ ተገለጸ::
የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ከከተማው ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ጋር በመሆን በከተማዋ ሊከሰቱ የሚችሉ የአደጋ ሥጋቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የነዋሪዎችን ሕይወትና ንብረት ከአደጋ ለመጠበቅ ተቋማት በሕግ የጸደቁትን የደህንነት መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ሊያሟሉ እንደሚገባ ተገልጿል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አሕመድ መሐመድ እንደገለጹት፣ በደንብ እና መመሪያ የነዋሪዎችን ሕይወትና ንብረት ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕግና መመሪያው ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ እስከ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ አወሳሰድ ድረስ ያለውን ኡደት የሚያካትት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘርሁን ተፈራ በበኩላቸው፣ ሕብረተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን መስፈርት በማያሟሉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
ተቋማት ከወዲሁ ከመመሪያው ውጪ ከሆኑ ድርጊቶች በመቆጠብ ሕግና መመሪያን አክብረው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተቋማትን ቸልተኝነት ወይም መስፈርቶችን ባለማሟላት በሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዳለባቸውም ተገልጿል።
በዓለሙ ኢላላ