ለነገ ስኬታችን መሠረቱ የዛሬው ህብረታችንና አንድነታችን ነው — የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

AMN -ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

የትላንት ድላችን፤የዛሬ ጥንካሬያችንና የነገ ተስፋችን ሚስጥር ህብር መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን ባህሎቻችንን ይበልጥ አጉልተን ለማውጣት አንድነታችንን ጠበቅ ማድረግ ይኖርብናል ሲል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ በ2019 ዓ.ም የሚከበሩ የህዝብ ክብረ በዓላትን አስመልክተው መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የስልጣኔ ባለቤት፤የብዝሃ ባህል፤ቋንቋና ማንነት የሚስተናገዱባት ሀገር ኢትዮጵያ ዜጎች ለዘመናት በአብሮነትና በህብር ተጋምደው ኖረዋል፡፡

ይህንኑ እሴት ለማስቀጠል በ2018 ዓ.ም የህዝብ ክብረ በዓላት በባህል ንቅናቄ እንዲታጀብ በማድረግ 46 ሚሊየን ዜጎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን እምቅ የባህል ምንጫቸውን አጉልተው ለማሳየትና ህብረ ብሄራዊ ቀለማቸውን እንዲለዋወጡ ለማድረግ በዜጎች መካከል መደጋገፍን፤ መተባበርን፤አብሮነትንና ወንድማማችነትን እንዲጠናክር መደረግ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

የተናጥል እና የጋራ እሴቶችን ይበልጥ ማጉላት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ወ/ሮ ነፊሳ በ2019 ዓ.ም የሚከበሩ የህዝብ ክብረ በዓላት ብሄራዊ መግባባትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ይበልጥ ጠንካራ መሰረት ያለው እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ባህል ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው እንዲሆንና ዜጎች በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑበት የተጀመረው ጥረትም መጠናከር አለበት ሲሉ ያወሱት ሚኒስትር ዲኤታዋ፣ የትላንት ድላችን፤ የዛሬ ጥንካሬያችንና የነገ ተስፋችን ሚስጥር ህብር መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን ባህሎቻችንን ይበልጥ አጉልተን ለማውጣት አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በሰላም መሰረት ላይ በመቆም ብልፅግናን ያረጋገጠች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያሉት ወ/ሮ ነፊሳ፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር አንዱ የአንዱን ባህል፤ ወግ፤ ማንነትና እሴትን ማክበርና ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ስንችል እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በደሴ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review