ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመላው ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት

You are currently viewing ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመላው ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት

AMN – ነሐሴ 8 /2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክና ባህል ሆኖ እየተከናወነ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መካሄድ ከጀመረ እነሆ ዛሬ ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም አንድ ወር አስቆጠረ፡፡

ሂደቱ በሀገራችን ሲከናወን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ፣ ለምክክር የቀረቡ አጀንዳዎች እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ እንዲሁም የሀገራችንን ብዙኃነት መሰረት ያደረጉ ፍላጎቶች በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጉባኤው የብዙዎች መነጋጋሪያ መሆኑ ለኮሚሽኑ አስገራሚ ሆኖ አልተገኘም፡፡

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያውያን የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከር ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ መከባበር፣ መደማመጥ እንዲሁም እያካበቱት ያለው ማህበራዊ ግንኙነት እጅጉን አመርቂ እና ተስፋ ሰጪም ነው፡፡

ይህ በሀገራችን አዲስ የሆነው የምክክር መድረክ ብዙዎች እንዲተዋወቁ፣ የአንተ ችግር የእኔ ነው እንዲባባሉ፣ ለነገ ሀገራቸው የሚጠቅም የጋራ ሃሳብ በመግባባት እንዲያፈልቁ እያስቻለ ይገኛል፡፡

ሂደቱ በኮሚሽኑ የአሠራር ሥነ-ዘዴ መሰረት አንዱን ምዕራፍ እየጨረሰ ወደ ሌላው ምዕራፍ ሲሸጋገር ቆይቶ አሁን ላይ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ደርሷል፡፡

በኮሚሽኑ ግምገማ መሰረት ያለፈው አንድ ወር የምክክር ሂደት ስኬታማ ሥራዎች የተሠሩበት፣ ምክክር ባህል እንዲሆን መሰረት የሚጥሉ አዳዲስ ጉዳዮች የታዩበት ነው፡፡

ይህ ማለት ግን ሂደቱ ሙሉ በሙሉ አልጋ በአልጋ ነበረ ማለት አይደለም፡፡ አለመግባባት የሚመስሉ ነገሮች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች አለመግባባት አለ ብለን ለተቀመጥን ወገኖች እንግዳ መሆን እንደሌለባቸው የኮሚሽኑ እምነት ነው፡፡

ኮሚሽኑ ካለው አሠራርና ልምድ በመነሳት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ምክክሩን ከማስጀመሩ በፊት በውል የተረዳው ጉዳይ በመሆኑ ጉዳዩ እንግዳ የመሰለው ለተመካካሪዎችና ወክለው ለመጡትት አካል ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ በዚህ ስጋት ላይ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች የሚያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃ ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩን ምን ያክል ውስብስብ እንደሚያደርገው ኮሚሽኑ ይረዳል፡፡

ለዚህ ነበር ኮሚሽኑ ህብረተሰቡን ከኮሚሽኑ ከሚወጡ መረጃዎች እንዲሁም በስፍራው የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ከሚያወጡት መረጃ ውጪ ካሉ መረጃዎች ራሱን በማቀብ ከሀሰተኛ መረጃዎች እንዲጠበቅ ሲያሳስብ የቆየው፡፡

አሁንም ምክክሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ተከትሎ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት መውጣታቸውን ስለሚቀጥሉ በድጋሚ መላው ኢትዮጵያውያን ኮሚሽኑ ከሚያወጣቸው መረጃዎች እንዲሁም በስፍራው የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ከሚያወጡት መረጃ ውጪ ያሉ መረጃዎችን ባለመከታተል ራሱን ከሀሰተኛ መረጃ እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ በድጋሚ ያሳስባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ጫፍ ያልደረሰ መረጃ በማጋራት በህዝብ ላይ ያልተገባ ብዥታና መደናገርን ከመፍጠር እንድትቆጠቡ ኮሚሽኑ በጥብቅ አሳስቧል።

መሰል ተግባራትን ኮሚሽኑ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሙያዊና ሥነ-ምግባራዊ ጥሰት እየፈጸሙ ያሉ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየሠረ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ይህ ክትትልና እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማሳሰቡን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review