ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተላለፈ መልዕከት

AMN – ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ከሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለፍጻሜ በመድረሱ መላው ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ አለን። ይህ ወቅት ለነገዋ ጠንካራ ኢትዮጵያ መሠረት የጣልንበት፣ የወደፊት እጣ ፈንታችንን በጋራ የቀረጽንበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

የዚህ የምክክር ሂደት ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ረጅም ጊዜያትን ያስቆጠሩ አለመግባባቶችና የግጭት መንስኤ በሆኑ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመመካከር በውይይት መፍትሔ መፈለግ ነው። ምክክሩ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው አካታችና አጠቃላይ ሀገራዊ መድረክ በመሆኑ በዓይነቱ ልዩ እና ታሪካዊ ያደርገዋል።

ይህ የምክክር ሂደት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት ራሱን የቻለና ገለልተኛ የፌደራል መንግሥት አካል ሆኖ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት bሕጋዊ ሥርዓትን የተመራ ነው። ኮሚሽኑን የሚመሩ አባላትም ተአማኒነት፣ ተቀባይነትና ገለልተኝነት በሚያረጋግጥ ግልጽ የሹመት ሂደት በምክር ቤቱ ተመርጠው ወደ ሥራ የተገባ ነው።

የምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማህበራት እና የዲያስፖራው ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ የተከናወነ ነው። ይህ አካታች የአጀንዳ አሰባሰብ እና የተሳታፊዎች ልየታ ሂደት በቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ደረጃ ድረስ በመውረድ የተከናወነ በመሆኑ የምክክሩን ተቀባይነትና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያረጋገጠ ነው።

ከሕዝብና ባለድርሻ አካላት በተሰበሰቡ አጀንዳዎች መሠረት ለጠቅላላው ጉባኤ የሚሆኑ 8 አንኳር ሀገራዊ አጀንዳዎች ተለይተው ከሐምሌ 8 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተካሄደው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ፣ ከመላው ሀገሪቱ የተወከሉ ከ4ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሰፊ ምክክር በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። በዚህ ታሪካዊ ሂደት የኃይልና የጦርነት ፖለቲካን በማስቀረት፣ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የተሻለ የውይይት ባህል በኢትዮጵያ መትከል ተችሏል።

ጉባኤው በስኬት ሲጠናቀቅ ለሀገራችን ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ በርካታ አበይት ምክረ-ሐሳቦችን በማፍለቅ ነው። እነዚህ ምክረ-ሐሳቦች ለቀጣይ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ ለሕገ-መንግሥታዊና ተቋማዊ ለውጦች እንዲሁም ለዘላቂ እርቅና ብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

የዚህ ምክክር ዋና ግብ ከትናንት ታሪካዊ ስብራቶቻችን በመማር፣ ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ሥርዓት በመገንባት ሰላሟ የተጠበቀና ብልፅግናዋ የተረጋገጠ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ነው። ስለሆነም መላው የሀገራችን ሕዝቦች፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የመንግሥት አካላት ከምክክሩ የተገኙ ውጤቶችን በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅ ወደ ተግባር እንዲተርጎሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

በመጨረሻም ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ አካላት እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሴና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review