የቅጠል ተራ የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ግንባታ መጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል

AMN – ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስጀመሩት መርካቶ ቅጠል ተራ አካባቢ እየተገነባ ያለው የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆች ግንባታ ፕሮጀክት 121 ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከፍተኛ አፈጻጸም ላይ ይገኛል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቦታው ላይ ተገኝቶ አፈጻጸሙ የደረሰበትን ደረጃ ምልከታ አድርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ በታቀደለት ፍጥነትና በጥብቅ ክትትል እየተካሄደ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ ኢንጂነር ጌታቸው ኃይሌ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ መሠረት ድንጋይ ከተጣለ 121 ቀናትን ማስቆጠሩን የገለጹት ኢንጂነር ጌታቸው፤ በአሁኑ ወቅት የውስጥና የውጭ ግንባታ ሥራዎች፣ እንዲሁም የለቀማ እና የፊኒሺንግ ሥራዎች ከፍተኛ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ሲመረቱ የነበሩ የእንጨት በሮች፣ የአሉሚኒየም መስኮቶች፣ ግሪሎች እና ጋርድ ሬይሎች በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው የመገጣጠሙ ስራም በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆኑን አማካሪ ኢንጂነሩ ተናግረዋል።

ለግቢው አጠቃላይ አገልግሎት የሚውል የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው 12 ሜትር የመሬት ክፍል ድንጋያማና አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ፣ ቀሪው ክፍል ለቁፋሮ የማያስቸግር በመሆኑ ይህ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ኢንጂነር ጌታቸው አመልክተዋል።

ሌላኛው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ኢንጂነር በለጠ ሃብቴ በበኩላቸው፣ የመስታወት መገጣጠም ሥራ በአንደኛው ብሎክ ላይ ብቻ 95 በመቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ከሕንፃዎቹ ግንባታ ጎን ለጎን የአማራጭ መንገድ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የልጆች መጫወቻ እንዲሁም የእግር ኳስ እና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች ግንባታ እየተከነወነ ነው።

በሌላ በኩል ግንባታቸው የመኖሪያ ቤቶቹ ነዋሪዎች ቤታቸው የተዋበ እንዲሆን የቀለም እና የተለያዩ የማጠናቀቂያ ስራዎች እና አጠቃላይ የውስጥ ዲዛይን ስራዎች ማራኪ እንዲሆኑ ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑን የባትኮን ኮንስትራክሽን ጀነራልማናጀር ኢንጂነር ይስሀቅ ባንተዋሉ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ በበኩላቸው በስራው ላይ ብቁ ባለሞያዎች መመደባቸው፣ በ24/7 የሥራ ባሕል መሰራቱ፣ በየቀኑ በሚደረግ የጥራት ቁጥጥር፣ ለግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች በቦታው ላይ ጥራታቸውን ጠብቀው መመረት መቻላቸውና ከንቲባ አዳነቸ አቤቤም ድንገተኛ ቅኝቶችን እና ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ ስለሚያደርጉ ለፕሮጀክቱ መፋጠን አስተዋኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review