ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህልን የተከለ ታሪካዊ ክስተት ነው- የምክክሩ ተሳታፊ የዲያስፖራ አባላት

AMN- ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት አዲስ የዲሞክራሲ ባህል እየተከሉ መሆኑን የገለጹት ከተለያዩ አህጉራት መተው ምክክሩን የተሳተፉ የዲያስፖራ አባላት፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የጥቂቶች ፍላጎት ሳይሆን የሕዝብን ሀሳብ ያዳመጠ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገለጹ።

ለኤ ኤም ኤን አስተያታቸውን የሰጡ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ የዲያስፖራ አባላት ሀገራዊ ምክክሩ ከትላንት ስህተቶች ተምሮ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርና ሰላም ለማስረከብ ትልቅ መሰረት የጣልንበት ነው ብለዋል።

ከአሜሪካ የመጡት አቶ ጋሻው ኢዳ፣ ከ130 ዓመታት በፊት አድዋ ላይ አባቶቻችን ነጻነታችንን እንዳስከበሩ ሁሉ፣ ዛሬ ከአራት ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ስለውደፊት ዕጣ ፈንታቸው መወያየታቸው ታሪክ የሰራ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።

ሌላዋ ከአሜሪካ የመጡት ተወያይ ማሜ ወርቁ በበኩላቸው፣ ምክክሩ ከጥቂት ሰዎች ጀምሮ እያደገ መጥቶ 4 ሺህ ሲደርስ የነበረው ሂደት ከሰፊ ውይይት በኋላ በዚህ ሁኔታ መጠናቀቁ ሂደቱ የላቀ ስኬት እንዳለው አሳይቷል ብለዋል።

ከእንግሊዝ የመጡት አቶ ዳዊት ዴንቴሞ፣ ሂደቱ የወደፊቱ ትውልድ ጠብመንጃ ማንሳቱን ትቶ ወንበር ስቦ የሚነጋገርበትን የተዘጋ በር የከፈተ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ወ/ሮ እልፍነሽ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ችግሮችን በጉልበት ሳይሆን በመመካከር መፍታት መቻሉ እንደ አድዋ እና አባይ ግድብ ሁሉ ኢትዮጵያውያን በአንድ መስመር የቆሙበት ትልቅ የለውጥ ማሳያ ነው ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ መንግሥት የሕዝቡን ችግር ከስር ጀምሮ አዳምጦ አጀንዳ የመሰብሰቡ ልምድ የዲሞክራሲ ትልቁ ልምምድ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review