AMN – ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የተጀመረው የአራዳ በጎነት መንደር የግንባታ ፕሮጀክት በከፍተኛ ፍጥነት ላይ መሆኑ ተገለጸ።
የአራዳ የበጎነት መንደር የአቅመ ደካሞችና የሀገር ባለውለታዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መጀመሩ ይታወሳል።
ቀደም ሲል የደሳሳ ጎጆዎች መገኛና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎችን በመቀየር፣ በርካታ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍ የታለመው ይህ ግዙፍ የበጎነት ተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ምዕራፍ ላይ መድረሱን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ባደረገው ቅኝት ታዝቧል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ ድርጅት ተወካይ ኢንጂነር በሪሁን ደርቤ ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተጀመረ 54 ቀናት ማስቆጠሩን አስታውቀዋል።
ግንባታው በሁለት ዙሮች የተከፈለ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር በሪሁን፣ አንደኛው ዙር ከብሎክ 1 እስከ 3 ያሉ ብሎኮች ግንባታ የተጀመረበት ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከብሎክ 4 እስከ 15 ያሉትን ብሎኮች አካቶ እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአንደኛው ዙር ግንባታቸው የተጀመሩት ስትራክቸራል ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሲሆን የብሎክ ዎርክ እና የልስን ሥራዎችም እስከ አምስተኛ ፎቅ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የግንባታ ሂደቱ በ24/7 የስራ ባሕል በከፍተኛ ጥራት እና ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር በሪሁን ፤ ይህ ስኬት እንዲመዘገብ የባለሙያዎች ቁርጠኝነት እና ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ስለግንባታው ሃሳብ የሰጡት ከአየሰና ባጫ ተቋራጭ ተወካይ ኃይለሚካኤል ዋቆሽ፣ የፊኒሺንግ፣ የቡሎኬት ግንባታ እና የልስን ስራዎችም በፍጥነት እየተከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ