በአዲስ አበባ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት በየዓመቱ 100 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ

AMN – ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ሁለገብ የቤት ልማት ስራዎች ከ496 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት መቻሉን አስታወቀ፡፡

ቢሮው በመጪዎቹ አምስት ዓመታትም በየዓመቱ 100 ሺህ ቤቶችን ገንብቶ ለቤት ፈላጊዎቹ ለማቅረብ እቅድ ይዞ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንዳገለጹት፤ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ በተከናወኑ ሁለገብ ስራዎች የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም ሰፊ ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የቤት ልማት ስራዎች ከ496 ሺህ በላይ ቤቶችን መገንባት መቻሉንም ሀላፊዋ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የመንግስትን ጥረት ብቻ ሳይገድብ፤ የግሉን ዘርፍ አሳታፊ በማድረግ ሪል ስቴቶች ወደ ልማቱ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎችና መደላደሎች መፈጠራቸውን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊዋ፣ ማህበራትን በማደራጀት፣ የ40/60 እና የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ጠባቂዎችን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀፍ ወደ ቤት ልማት እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።

በመንግስትና በግል አጋርነት አዲስ እይታ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት ማፍራታቸውን ጠቅሰው፤ ከመንግስት በጀት ግንባታዎች ጎንለጎን ሰፊ የልማት ሞዳሊቲዎች ወደ ተግባር በመገባታቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 496 ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን መገንባት እንደተቻለ አስረድተዋል።

የግሉን ዘርፍ በስፋት በማሳተፍ የነዋሪዎችን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የመጪዎቹ አምስት ዓመታት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችና እቅዶች መካከል አንዱ መሆኑንም ሀላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review