AMN – ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር እና ለኢኮኖሚያዊ ማንሰራራት ወሳኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባሕር በር ጥያቄ የማንንም ጎረቤት ሃገር ሉዓላዊነት የማይነካ በፍትሃዊነት የመጠቀም እና መተንፈሻ በር የማግኘት መብት በታሪክም ሆነ በህግ ድጋፍ ያለው የህልውና ጥያቄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለውን ለውጥ ዘላቂ ከማድረግ ባለፈ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት እና ለቀጣናዊ ትስስር ትርጉም ያለው መደላድል ይፈጥራል፡፡
ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ለወደብ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ በሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መቆየቱም የሚታበል አይደለም፡፡
አሁን ላይ የባህር በር ጥያቄዋን በገሃድ ማንሳቷና ይህ ጥያቄዋም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ማዳበርን ያሳያል፡፡
የባህር በር ጥያቄ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉልህ ሚና የሚጫወት ሲሆን ይሄን የባህር በር ጥያቄ አስፈላጊነት ተረድቶ የአሁኑ ትውልድም ጥያቄ በማቅረብ ቆራጥ አቋሙን አሳይቷል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የባህር በር አጠቃቀም ስምምነቶችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

አንዳንዶች ግን ከፍተኛ ጂኦፖለቲካዊ ፍጥጫ ባለበት የቀይ ባሕር ቀጠና ኢትዮጵያ የመልክአ ምድር እስረኛ እንድትሆን በርካታ ሲራዎችን ሲሸርቡ ቆይተዋል ፣ አሁንም እየሸረቡ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባህር በር ጉዳይን አስመልክቶ ባንድ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ውስጥ ሆና መቀጠል እንደማትችል መግለጻቸው ይታወሳል።
የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ የባህር በር ባለቤትነት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሻምበል ምህረት