የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች ልማትን እያረጋገጠች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች ልማትን እያረጋገጠች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች ልማትን እያረጋገጠች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤

የስደተኞች ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወነውን ውጤታማ ተቋማዊ ሪፎርም በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ተመልክተዋል፡፡

ይህ ሪፎርም የሥራ ቦታን ከማሻሻል ባለፈ፣ የሥራ ባህልን፣ የአገልግሎት ጥራትንና ተቋማዊ ዐቅምን የሚያጎለብት ለውጥ ነውም ብለዋል።

የአገልግሎቱ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ስደተኞች በመቀናጀት በዋና መሥሪያ ቤቱ፣ በ6 ክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በ27 መጠለያ ጣቢያዎች ያከናወኑት ሥራ፣ በራስ አቅም ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ጥሩ ተሞክሮ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም የመደመር መንግሥት የግብርና እመርታ ማሳያ የሆነውን የሌማት ትሩፋትን በመጠቀም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብና በተለያዩ የዕጽዋት ልማት ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች፣ ተቋማዊ ሪፎርም የሚለካው በተሻለ የሥራ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሚፈጥረው ምርታማነትና ውጤት ጭምር መሆኑን ያሳያሉ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ።

ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል፣ መብትና ክብራቸውን በማስጠበቅ ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በማስተሣሠር በልማት ዕድሎች ተጠቃሚ እያደረገች ነው ያሉ ሲሆን ስደተኞቹ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት ፤ በራስ ዐቅም የሚመጣ ለውጥ የተቋምን ዐቅም ያጎለብታል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገርን ዐቅም ይገነባል፡፡ በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ያየነው ስኬታማ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review