የሀገራዊ ምክክር የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር የቀየረ አዲስ ምዕራፍ ነው

You are currently viewing የሀገራዊ ምክክር የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር የቀየረ አዲስ ምዕራፍ ነው
  • Post category:ፖለቲካ

AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በመጠፋፋት፣ በመገፋፋት እና በሴራ ትንተና ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ አውድ የቀየረ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፣ ይህ አዲስ ሀገራዊ እሳቤ እና ጉዞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከጠመንጃ አፈሙዝ እና ከኃይል አማራጭ አላቆ፣ ለሀገር ሰላምን በሚያሰፍን እና በመነጋገር ውስጥ መደማመጥ እንዳለም ፍንጭ የሰጠ ሆኗል ብለዋል።

የህዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሕዝብን ያቀራረበ፣ ማህበራዊ መስተጋብርንም በውል የገለጸ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

ምክክሩ በተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና እሳቤ ለተለያዩ መርሆችም የሚገዙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ ሀገርን ያስቀደመ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ንግግር ያደረጉ ዘንድ እድልን ፈጥሯልም ብለዋል።

የወሎ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ነጻነት ጣሰው፣ ምክክሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ለኢትዮጵያም አዋጭ መንገድን መቀየሻ እና ከችግር መውጫ አመላካች ሀሳቦችን ማመንጨት የተቻለበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገርን መልክ ተላብሶ በልዩነት ውስጥ አንድነትን አክብሮ አካታችነቱንም በውል አረጋግጦ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ከጠመንጃ ባለፈ ንግግርን ያስቀደመ፣ ከስሜት በተሻገረ ምክንያታዊነትን ያስቀደመ ትውልድን ለመፍጠር እና በቀጣይ ጠንካራ ሀገርን እውን ለማድረግ ዛሬ ላይ መሰረት ተጥሏል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ፣ ይህ ለዛሬው ትውልድ ትልቅ የድል አሻራ ለነገ ትውልድ ደግሞ ታሪካዊ ቅርስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተመስገን ይመር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review