በ8 አመታት ከ56.2 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ የጻፈቸው – ኢትዮጵያ

AMN – ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብሳሪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

መርሃ ግብሩ የተጀመረው የመሬት መጎሳቆልን፤ የድርቅ ተጋላጭነትን፤ የደንና የብዝሀ ህይወት መጨፍጨፍን፤ የውሀ አካላቶች መድረቅን፤ የወንዞች በደለል መሞላትን ብሎም የወጣቶች ስደትን ለመከላከል ታስቦ ነው፡፡

በመርኃ ግብሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ 50 ቢሊየን ችግኝን በማህበረሰብ ተሳትፎ ለመትከል ታቅዶ የተጀመረ ሲሆን በ8 ዓመታት ውስጥ ከ56.2 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በዘርፉ በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ በ2018 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብቻ ከ8.2 ቢሊየን በላይ ችግኞች በሃገር አቀፍ ደረጃ ተተክለዋል፡፡

በአጠቃላይ ከተተከሉ ችግኞች ከ3 ቢሊየን በላይ የሚሆኑት በአንድ ጀምበር የተተከሉ መሆናቸው ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ እንድትጽፍ አስችሏታል፡፡

ከከተከሉ ችግኞች 65 እጅ የሚሆኑት የጥምር ደን ግብርና እንደ ፍራፍሬ፤ ቡናና እና የመኖ ዝርያዎች ሲሆኑ 35 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ የደን ዝርያዎች ናቸው፡፡

እስካሁን በተሰራ ስራ የደን መጨፍጨፍ ከ92 ሺህ ወደ 27 ሺህ ሄክታር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን በእርሻ ማሳ ያለ የአፈር ብክለት በአመት ከ130 ቶን ወደ 54 ቶን በሄክታር ቀንሷል፡፡

በአመት መቀነሱና እንዲሁም ወደ ውሀ አካላት የሚገባ የአፈር ደለልም በአመት ከ1.9 ቢሊየን ቶን ወደ 208 ሚሊየን ቶን ቀንሷል፡፡

ወደ 2.6 ሚሊየን ለሚጠጉ ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ በበርካታ አካባቢዎች የፍራፍሬና የደን ክላስተሮች የተፈጠሩ ሲሆን ለገበሬውም ዋንኛ የኢኮኖሚ ዋስትና እየሆነ ከመምጣቱም ባሻገር ወጣቱ ሀገሩን እንዲወድ፤ እንዲቆረቆርና እንዲተባበር እያደረገ ይገኛል፡፡

መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር ትልቅ የልማት መርሀ ግብር ቀርጾ መተግበር እንደሚቻል ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበትና ለዓለምም ምሳሌ የሆነችበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እና የበረሃማነት ሰለባ ከመሆን አልፋ የመፍትሄው አካል በመሆን ለተቀረው ዓለም አርአያ ሆናለች፡፡

ይህ ታላቅ የልማት ድል እንዲሳካም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እስከ ታችኛው የመንግስት አደረጃጀት ድረስ ያለው አመራር በቁርጠኝነት ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች በአመት ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማንቀሳቀስ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዲሳተፉ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review