AMN- መስከረም 9/2019 ዓ.ም
የወላይታ ሕዝብ ዘመን መለወጫ ”ጊፋታ”፤ የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የዕርቅ እና የመረዳዳት እሴቶችን የሚያጎላ የአንድነት መሠረት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የአንድነት መሠረት እና የጋራ አብሮነት መገለጫ የሆነው የጊፋታ በዓል አንዱ ነው።
የወላይታ ዞን በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች የሚገኙበት ሲሆን ጊፋታ በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡
በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የወላይታ ብሔር ማንነት መገለጫ፤ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡
ጊፋታ ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከክረምት ወደ ልምላሜ መሻገርን የሚገልጽ ሲሆን በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ እንደሆነም ይገለጻል፡፡
በዚህም አባቶች፣ እናቶች እንዲሁም ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሕጻናትም ጭምርሳ በጊፋታ በዓል ዝግጅት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡
የዘመን መለወጥን የሚያበስረው ጊፋታ በዓል የራሱ የሆነ የአከባበር ስርዓትም አለው፡፡ በጊፋታ በዓል አከባበር ወቅት መልካም ምኞትን ጨምሮ የአባቶች ምርቃት፤ የሩጫ ውድድር እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ስርዓቶች ይከወናሉ።
ከእነዚህ የበዓሉ ስርዓቶች መካከል የጊፋታ ዋዜማ ሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ትናንት በታላቅ ድምቀት መካሄዱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የወላይታ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስሞዖን ስላሎ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት ፤ የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በዩኔስኮ በመመዝገቡ ወላይታን በዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና አለው።
የዘንድሮው የጊፋታ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ የሚከበር የመጀመሪያው ዓመት በመሆኑ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህም የሀገራችንን የጥንታዊ ባህል መነሻነት በጉልህ የሚያሳይ የጋራ ሀብት ነው፡፡
የጊፋታ በዓል ነገ “የትውልድ ቅርስን እንጠብቅ፣ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል” በሚል መሪ ሃሳብ በአደባባይ በድምቀት ይከበራል። የጊፋታ በዓል ማንነትን እና ታሪክን ለወጣቱ ትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው።
ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚከበረው ጊፋታ የህዝብ አንድነትን ከማጠናከርና የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር በቱሪዝም መስህብነት የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው፡፡
በተመሳሳይ ጊፋታ ፍቅርና አንድነት የሚጠናከርበት፤ ተራርቀው የነበሩ የቤተሰብ አባላት ዘመድ አዝማድና ጓደኞች የሚገናኙበትና ፍቅራቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም የመተጋገዝ ባሕልን የሚያሳድጉበት ነው።
የጊፋታ በዓል የወላይታ ህዝብ የሰላም እና የጋራ አብሮነት መገለጫ በመሆኑ በዓሉ የህዝብን አብሮነት በሚያጎላ መንገድ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል፡፡
የሻምበል ምህረት