ከ”በጎነት መንደር” እስከ “ተስፋ ብርሃን”

You are currently viewing ከ”በጎነት መንደር” እስከ “ተስፋ ብርሃን”

AMN- መስከረም 10/2019 ዓ.ም

የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከዘመናዊ የከተማ መሠረተ ልማት ባለፈ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር የሚመልሱና ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍኑ በርካታ ስራዎችን በማከናወን የማንሰራራት ተምሳሌት መሆኗን በተግባር እያሳየች ነው፡፡

ለዚህ የከተማዋ አዲስ ገጽታ እና የሰው ተኮር ልማት ዋነኛ ማሳያ ከሆኑት ግዙፍ ማህበራዊ ፕሮጀክቶች መካከል፣ የ”በጎነት መንደር” ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች እና የ”ተስፋ ብርሃን” የምገባ ማዕከላት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

“የበጎነት መንደር”፤ ለሰው ልጅ ክብር ለማይመቹ እና ለከፋ የጤናና ማኅበራዊ ችግር አጋላጭ ለነበሩ ደሳሳ አካባቢዎች ምትክ፤ ስፍራዎቹን እንደ አዲስ በማልማት የከተማዋን አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ኑሮ እያሻሻለ ነው፡፡

ይህ ማኅበራዊ ፕሮጀክት ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ባለፈ፤ ለኑሮ ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን በዘላቂነት ማቋቋም ችሏል፡፡

በተጨማሪ የበጎነት መንደሩ ነዋሪዎች ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት እንዲችሉ ታስቦ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያን ጨምሮ መሰል መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል፡፡

በሌላ በኩል በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ለማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ዜጎች እፎይታን የሰጠው “የተስፋ ብርሃን” የምገባ ማዕከል የከተማዋ ሌላኛው የሰው ተኮር ልማት ማሳያ ነው፡፡

በመዲናዋ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተገነቡት እነዚህ ማዕከላት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ በጎ አድራጊ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር በቀን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

ይህም የዜጎችን ጤናና ህይወት ከመታደግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች አዲስ የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ60 ሺህ በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ማህበራዊ ፍትህን የሚያሰፍኑ እና በቀጥታ የሰውን ልጅ ህይወት ለማሻሻል ያለሙ “ሰው ተኮር” ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በተለይም ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን መንግሥት ከበጎ ፈቃደኞችና ከባለሀብቶች ጋር በአጋርነት መተግበሩ፣ የኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ማኅበራዊ እሴት በይበልጥ የሚያጎለብት ነው፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review