AMN – መስከረም 10/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች: ሃይማኖቶች: ቋንቋዎች: ባህሎችና ማንነቶች መገኛ ነች።
በአብሮነትና በወንድማማችነት መንፈስ ላይ የተገነባዉ ይህ ብዝሃነት ለሀገሪቱ ማህበራዊ: ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ትልቅ ጸጋና መሠረት ነዉ።
ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ያላቸዉ ህዝቦች ሲሆኑ እንደ እድር፣ እቁብ እና ማህበር ባሉ ሃገር በቀል ባህላዊ አደረጃጀቶች ያላቸዉን የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠናክራሉ።
የተጣላን ማስታረቅ: የተቸገረን መርዳት: የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በአላትን በጋራ ማክበር ሌላኛዉ የማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከሪያ እሴት ነዉ።
እነዚህ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የትብብር: የአብሮነትና የወንድማማችነት መንፈስን የሚፈጥሩ: ልዩነትንና የመከፋፈልን መንፈስን የሚያክሙ ናቸዉ።
አብሮ መብላት: መጠጣት: የተቸገረን መርዳት: የተጣላን ማስታረቅ: በአላትን በጋራ ማክበር: መረዳዳት እና መከባበር በኢትዮያዊያን ዘንድ ትልቅ ከበሬታ አለዉ።
በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዕርቅና የፍትህ ሥርዓቶችም በደል ፈጻሚውን በመቅጣት ብቻ የሚገቱ ሳይሆኑ፣ የተሰበረውን ማህበራዊ ትስስር በመጠገን ሁለቱን ወገኖች በእርቅና በፍቅር የሚመልሱ ናቸው።

ይህ ባህል ህዝቦች ያለፉባቸውን ቁስሎች በመፈወስ የጋራ የኢትዮጵያዊነት ትርክት አካል እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ባህላዊ የሰላም እሴቶች ህብረተሰቡ ተከባብሮና ተቻችሎ እንዲኖር፣ ፍትህ እንዲሰፍን እና ማህበራዊ ኑሮው የተረጋጋ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
ጠንካራ ማህበራዊ: ባህላዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮችና ትስስሮች ብሔራዊ ትርክትን ከመገንባት ረገድ ያላቸዉ ሚናም የጎላ ነዉ።
ማህበራዊ መስተጋብሮቹ የዜጎችን የብሄር: የሃይማኖት: የባህል: የቋንቋና የማንነት መብት የሚያከብሩ መሆናቸዉ ደግሞ ልዩ ያደርጋቸዋል።
እነዚህ ኩሩ ሃገር በቀል ባህላዊ እሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ መልካም ግንኙነቶችን ይበልጥ የሚያጠክሩ ናቸዉ እንጂ: ልዩነቶችን እንደ ስጋት የሚቆጥሩ አይደሉም።
በማህበራዊ ኑሮ ዉስጥ ከጥላቻና ከጥርጣሬ ነጻ ሆኖ በመከባበርና በይቅርታ መንፈስ መኖር የሚቻለዉ ነባሮቹን የሰላም እና የአብሮነት እሴቶችን ስንጠቀምና ስናዳብር ነው።
የኢትዮጵያ ባህልና እሴቶች የሀገሪቱ የማንነት ማህተም፣ የሰላም፣ የዕርቅ እና የአንድነት መገለጫዎች ናቸው።
እነዚህን የቆዩና ውድ እሴቶች ማጠናከርና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊት እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመገንባት ቁልፍ መፍትሄ ነው።
እነዚህ ባህላዊ እሴቶች ከግጭትና ከልዩነት ይልቅ መመካከርን: መነጋገርን እና ይቅርታን የሚያስቀድሙ መሆናቸዉ ደግሞ ብሄራዊ መግባባትን ከመገንባት ረገድ ያላቸዉ ሚና የላቀ ነዉ።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ