ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጀምራል

You are currently viewing ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጀምራል

AMN- ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም

ለ21ኛ ጊዜ የሚከናወነው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጀምራል።

በአሜሪካ ኦሪገን ሃይዋርድ ፊልድ በሚደረገው የዘንድሮ ውድድር ላይ ከ147 ሀገራት የተውጣጡ 1,800 አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከእነዚህ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በውድድሩ ያላትን ታሪክ ለማስቀጠል አትሌቶቿን ወደ ስፍራው ልካለች።

ኢትዮጵያ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት። ከዚህ ቀደም በተከናወኑ ውድድሮች 52 የወርቅ ፣ 53 የብር እንዲሁም 34 የነሃስ በአጠቃላይ 139 ሜዳልያዎችን በማግኘት የምንጊዜም ሦስተኛዋ ውጤታማ ሀገር ናት። ኢትዮጵያን የሚበልጡት አሜሪካ እና ኬንያ ብቻ ናቸው።

ከሁለት ዓመት በፊት በፔሩ ሊማ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች ድንቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለው ነበር። 6 ወርቅ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎችን በማምጣት ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ነበር ያጠናቀቁት።

ኢትዮጵያ ዘንድሮም ውጤቷን ለማስጠበቅ በ5000 ሜትር ፣ 3000 ሜትር ፣ 1500 ሜትር ፣ 800 ሜትር እንዲሁም በእርምጃ (በሁለቱም ፆታዎች) ፣ 3000 ሜትር መሰናክል (በሴቶች) ፣ 400 ሜትር (በሴቶች) ትሳተፋለች።

ለአምስት ቀናት የሚቆየው ውድድር ዛሬ ሲጀምር ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ቀን በ800 ሜትር በሁለቱም ፆታ እንዲሁም በ3000 ሜትር ሴቶች የማጣሪያ እንዲሁም በሁለቱም ፆታ በ5000 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ላይ ትካፈላለች።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review