በኅብረ ብሄራዊ አንድነት ጽኑ መሰረት ላይ የተገነባችው – ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ

AMN- መስከረም 11/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖቶች ፣ባህሎች ፣ ቋንቋዎችና ማንነቶች መገኛ ስትሆን ህዝቦቿም ተከባብረውና ተቻችለው በመኖር ይታወቃሉ፡፡

ኢትዮጵያ በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁማና ተሻግራ፤ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረችም ሀገር ነች፡፡

ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ በጎረቤት ሃገራት፤ በአፍሪካና በተቀረው ዓለም በሰለም ማስከበር እና በሌሎች ሰብዓዊና የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ለተቀረው ዓለም አጋርነቷን አስመስክራለች፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ውክልና ያላት ሃገር ስትሆን ከራሷ አልፎ፤ የጥቁር ህዝቦችና የተቀረው ዓለም ህዝብ ነጻነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ድምጽ እስከመሆን ደርሳለች፡፡

ኢትዮጵያ በልማቱም ዘርፍ ቢሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የገነባች ሀገር ስትሆን፤ በተፈጥሮ ባገኘችው የውሃ ሃብቷ ቀጣናውን በሃይል በማስተሳሰር የልማት ተምሳሌት ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ባገኘችው የውሃ ሃብቷ እንዳትጠቀም፤ እንዳትለማና በኢኮኖሚ ከተቀረው ዓለም ጎን እንዳትሰለፍ በርካታ ጫናዎች ቢደረግባትም እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች በጽናት ተሻግራ ህልሟን እውን አድርጋለች፡፡

በአንድ ወቅት የቀይ ባህርና የወደብ ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ፤ በታሪካዊ ጠላቶቿና በውስጥ ተላላኪዎች ሴራ የባህር በር ብታጣም ይህንኑ መብቷን ለማስከበር ጥረት በማድግ ላይ ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት የተሻገረች ስትሆን ይህም የጥንካሬዋ ምንጭና የታላቅነቷ መሰረት ሆኗል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review