ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ቀጣናዊ ትስስር እውን ለማድረግ የባሕር በር ማግኘት ይገባታል

You are currently viewing ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ቀጣናዊ ትስስር እውን ለማድረግ የባሕር በር ማግኘት ይገባታል

AMN መስከረም 14/ 2019

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ቀጣናዊ ትስስር እውን ለማድረግ አስተማማኝና ዘላቂ የባሕር በር ማግኘት እንደሚገባት ፕሬዝደንት አቶ ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ በኒው ዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በጋራ ደኀንነት እና በእውነተኛ እኩልነት ላይ የተመሠረተ ባለብዙ ወገን ግንኙነት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች አገር እንደመሆኗ መጠን ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጡት ፕሬዝዳንቱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካን በሚመጥን መልኩ በአስቸኳይ መዋቅራዊ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 1.6 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በምክር ቤቱ ተገቢውን ውክልና አለማግኘቷ የፍትህና የሞራል ጥያቄ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል።

የኢትዮጵያን አገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎችና ስኬቶችን በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ፡-የአየር ንብረት ለውጥና ኮፕ-32 (COP-32)፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በህዳር 2027 የሚካሄደውን የኮፕ-32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጸው፣ የዓለም መሪዎች በጉባኤው ላይ ተገኝተው አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ እስካሁን 56 ቢሊዮን ችግኞች መተከላታቸውንና ይህም በዓመት 9 ቢሊዮን ቶን ካርቦን የመምጠጥ አቅም እንዳስገኘ ገልጸዋል።

የምግብ ዋስትናና ታዳሽ ኃይል፡ አገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት ወደ አፍሪካ ትልቁ የስንዴ አምራችነት መሸጋገሯን በመጥቀስ አፍሪካ ራሷን መመገብ እንደምትችል ማረጋገጧን ተናግረዋል።

በታዳሽ ኃይል ዘርፍም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ እስከ 2030 እ.ኤ.አ. ድረስ 13,000 ሜጋ ዋት ለማመንጨትና ለምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከልነት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት እድገት፡ የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም፣ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እና በ12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና መሳካት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።

ፕሬዝደንት ታዬ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለሚደረጉ የኢኮኖሚ ትስስር ሥራዎች በትጋት እየሰራች መሆኗንና በአንዳንድ አፈራሽ የውጭ አካላት የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችን በትዕግስት አልፋ አገራዊ እድገቷ ላይ ትኩረት ማድረጓን ገልጸዋል።

የሱዳንን ቀውስ በተመለከተም ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው በሱዳናውያን ባለቤትነትና መሪነት በሚደረግ የሰላም ሂደት ብቻ እንደሆነ አቋማቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ፕሬዝደንቱ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ቀጣናዊ ትስስር እውን ለማድረግ አስተማማኝና ዘላቂ የባሕር በር ማግኘት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም አገሪቱ ይህንን ፍላጎቷን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማሳካት እየሰራች መሆኗን አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review