አዲስ አበባ በአፍሪካ ካሉ ከተሞች ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ሆናለች

You are currently viewing አዲስ አበባ በአፍሪካ ካሉ ከተሞች ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ሆናለች

AMN – መስከረም 14/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ፣ ሃይማኖቶች የተለያዩ ማንነቶች ፣ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላትና የውጭ ሃገር ዜጎች የሚኖሩባት የአፍሪካ መዲና ነች፡፡

መዲናዋ በብዝሃነትና በህብር ያጌጠች ብቻ ሳትሆን የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ዜጎች በነጻነትና በደስታ የሚኖሩባት ሰላማዊት ከተማ መሆኗ ልዩ ያደርጋታል፡፡

የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በድምቀት የሚከበሩባት መዲና መሆኗ ደግሞ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች የተለያዩ ኩነቶችን በቅርበት እንዲመለከቱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮላቸዋል፡፡

በተለይ የመስከረም ወር እንደ ጎቤ ፣ ሽኖዬ ፣ ሻደይ ፣ አሸንድዬ ፣ ሶለል ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀልና ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በአላትና ትዕይንቶች የሚከበሩባት በመሆኗ የቱሪስቶች ፍሰት ከወትሮው እንደሚጨምር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በመዲናዋ የሚኖሩትን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከተለያዩ የአለም ሃገራት የሚመጡ ቱሪስቶች የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ባህላዊ አልባሳት ከመልበሳቸው ፣ ምግቦችን እና መጠጦችን ከማጣጣማቸውም በላይ እጅግ በሚያምሩ ሃገርኛ ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች ላይ በመሳተፍ የማይረሳ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜአት ወዲህ በአደባባይ በሚከበሩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በአላት ላይ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አልባሳት የሚጠቀሙ የውጭ ሃገራት ዜጎችን መመልከት የተለመደ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ በህብርና በህብረብሄራዊነት የደመቀች ሃገር ለመሆኗ ትልቅ ማረጋገጫ ነው፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከጥቂት አመታት ወዲህ በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የተገነቡት የቱሪዝም ማዳረሻዎች ፣ ፓርኮች ፣ የቅርስ ማዕከላት ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች እና ሆቴሎች ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡

በተገነቡት መሰረተ ልማቶች አዲስ አበባ አሁን ላይ ቱሪስቶች የሚተላለፉባት ብቻ ሳትሆን ውለው የሚያድሩባት፤ የሚቆዩባትና ደግመው ተመልሰው ለመቆየት የሚናፍቋት መዲና ለመሆን በቅታለች፡፡

የመዲናዋ አስተማማኝ ሰላም ቱሪስቶች ቀን ብቻ ሳይሆን በምሽት እንዲዝናኑ ፣ መዲናዋን እንዲጎበኙና የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

አዲስ አበባን ብሎም ኢትዮጵያ የጎበኙ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስለ ሀገሪቱ ምቹ የቱሪዝም ማዕከልነት መመስከራቸው ኢትዮጵያን ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ የተሻለ ዕድል ፈጥሯል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review