AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት አበክረው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምዕመናን ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጎብኚዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የመስቀል በዓል በመከራ መስቀል ህይወቱን አሳልፎ ህይወታችንን የማያልፍ ህይወት ያደረገውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናስብበት ነው ብለዋል።

ክርስቶስ በመስቀሉ ያስተማረንን ፍቅር እና ዋጋ በህይወታችን ልንተገብረው ይገባል ያሉት ፓትሪያርኩ መስቀል የሚያስተምረን ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርታን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ሰላምና አንድነት መረጋጋጥ አበክረን ልንሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ብጹዕነታቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለመስቀል በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡