AMN – መስከረም 17/2019 ዓ.ም

በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ መስቀል ከሃይማኖታዊ ክንውን የላቀ፤ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና የዘመን መለወጫ ትርጉም የተሰጠው ታላቅ በዓል ነው።
ማህበረሰቡ ይህንን ዕለት ከየትኛውም ክብረ በዓል አስበልጦ በላቀ ድምቀትና ፍቅር ያከብረዋል።
በዚህም የተነሳ፣ መላው የጉራጌ ሕዝብ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገራት ወደ ትውልድ ቀዬው ይመጣል፤ በዓሉንም ከቤተሰቡና ከወገኑ ጋር በድምቀት ያሳልፋል።

በዓሉ ከመድረሱ ሳምንታት በፊት ጀምሮ መንደሮችና ቤቶች ይጸዳሉ፤ ይታደሳሉ። ለዕለቱ የሚሆን ቆጮ፣ ንጹህ ቅቤ እና የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች በስፋት ይዘጋጃሉ።
መስቀል አለመግባባቶች የሚረሱበት፣ ዕዳ የሚሠረዝበት እና የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት ታላቅ የፍቅር ወቅት ነው።
መስከረም 16 ቀን በአደባባይ በሚከናወነው የደመራ ስነ-ስርዓት አባቶችና ሽማግሌዎች ስለ ሰላም እና አንድነት የሚመርቁበት፣ የሰንጋ ሻኛ በመዳሰስም ለሀገር ሰላም የሚጸለይበት ዕለት ነው።
ማህበረሰቡ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ከብቶች በማረድ እንግዶችን ያስተናግዳል፤ ለወለደች አራስ «ሸሉዳ» እና ለተገረዙ ልጆች «ጭቅና» ስጋን በመስጠት አብሮነቱን ያሳያል።
ወጣቶችና አዛውንት ደመራ ለማብራት በወጡበት ወቅት በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና በንግድ ስራዎች ላይ ይመክራሉ፤ ጎልማሶችም ከአባቶች ኃላፊነት ይረከባሉ።
ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 በሚኖረው ባህላዊ «የአዳብና» ጨዋታ ወጣቶች ሎሚ፣ ብርቱካን እና ሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ ጓደኛ የሚመርጡበትና ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት የሚጥሉበት ድንቅ ገጽታ አለው።
ይህ ታላቅ በዓል ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ማህበራዊ ችግሮች የሚፈቱበት እና ባህሉ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍበት ትልቅ የማንነት መገለጫ ነው።
የጉራጌ ሕዝብ መስቀልን ከማክበር ባለፈ፣ ይህ በዓል በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰስ የባህል ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ማህበረሰቦች አንዱ መሆኑ በታሪክ የሚዘከር ነው።
በበረከት ጌታቸው