የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም ቁልፍ ዘርፎች ያካተተና ዘላቂነት ያለው ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም ቁልፍ ዘርፎች ያካተተና ዘላቂነት ያለው ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በቱሪዝም ዘርፍ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ሁሉንም ቁልፍ ዘርፎች ያካተተና ዘላቂነት ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሐሮ ደንዲ ሎጅ መመረቁን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ ቁጥር አንድ ሀገር እንደምትሆን መተንበያቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ተቋማቱ ግምት ኢትዮጵያ ከ9 በመቶ በላይ እድገት የምታረጋግጥ ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንደምትሆንም ነው የጠቀሱት።

ይህ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ግልጽ ስትራቴጂን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት የተገኘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ብዙ ሰዎች የእኛን ስራ በቱሪዝም ብቻ ለመለካት ይሞክራሉ፣ ይሄ ስህተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ እድገቱ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድን እና በቱሪዝም ዘርፎች የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ድምር ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስት የት ጋር ምን መስራት እንዳለበት አውቆ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም መሠረተ ልማትን ከምርትና ምርታማነት ጋር በማስተሳሰር ረገድ የተሰሩ ስራዎች ለኢኮኖሚው አስተማማኝ መሰረት መጣላቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችን ደም ብቻ ሳይሆን በእኛም ላብ ትገነባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አባቶች በጀግንነት ሀገርን ጠብቀው እንዳቆዩ ሁሉ አሁንም በፖሊሲና በላብ ሀገርን የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞም ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያምኑበት ልክ እየተረጋገጠ መሆኑንና ይህም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በንግግራቸው ጠቁመዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review