AMN- መስከረም 23/2019 ዓ.ም
በሆረ ፊንፊኔ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የታደሙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በበዓሉ አከባበር፣ በህዝቡ የእንግዳ ተቀባይነት እና በአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን እድገት መደመማቸውን ገለጹ።
ከኔዘርላንድስ የመጡ ታዳሚ በበዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ በበዓሉ የታየው ደስታ፣ የኦሮሞ ባህል ውበት፣ ህዝቡ ያሳየው ፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት እንዲሁም የአልባሳቱ ውበት ከጠበቁት በላይ እና የማይረሳ አጋጣሚ እንደሆነላቸው ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
አክለውም ከጥቂት ዓመታት በፊት አዲስ አበባን መጥተው መጎብኘታቸውን እና ከአሁኑ ጋር ያለውን ሲያነጻጽሩ አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠችና ዘመናዊ እየሆነች መምጣቷን ጠቁመው ፣ ከተማዋ ይህ ትልቅ የእድገት ደረጃ የሚገባት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌሎች የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በበኩላቸው፣ በከተማዋ በየቦታው የሚታዩ የግንባታና የልማት እንቅስቃሴዎች ከዓለም ሁለገብ ከተሞች በተለየ ፍጥነት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ የከተማዋን ገጽታ በፍጥነት እየቀየሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በበዓሉ የተገኙት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የኢሬቻ በዓል የምስጋና እና የሰላም በዓል በመሆኑ አድናቆታቸውን በመግለጽ፣ ለህዝቡና ለሀገሪቱ መልካም የምስጋና በዓል ይሆን ዘንድ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአስማረ መኮንን