AMN- ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ለግልና ለመንግስት ተቋማት የቅጥር ጥበቃ አባላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር፤ የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ ሰላም ለማስጠበቅ የቅጥር ጥበቃ አባላት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በተለይም የሀገርን ብሎም የአዲስ አበባን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን እቅድ በማክሸፍ ረገድ አባላቱ የሰሩት ስራ ለሰላም መሰረት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ሰላም ለማደፍረስና የሀገርን ገፅታ ለማጠልሸት የሚሰሩ ሀይሎችን ተልዕኮ ከውስጥም ከውጭም በተጠንቀቅ መጠበቅ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል አቶ ተስፋዬ ደንድር።

በጋራ መኖሪያ መንደሮች አካባቢ የሚፈፀሙ የመኪና፣ የቤት እቃ ስርቆትና ሌሎች መሰል ህገ ወጥ ተግባራትን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በትብብር መስራት እንደሚገባ አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል።
ከ25 ሺህ 400 በላይ የግልና የመንግስት ተቋማት የቅጥር ጥበቃ አባላት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን የዛሬው የመጀመሪያው ዙር መሆኑ ተመላክቷል።
በንጉሱ በቃሉ
#ትልቅሃገር#ትልቅህዝብ#ታላቅርዕይ#አዲስሚዲያኔትዎርክ#የትዉልድድምጽ#አዲስአበባ#ኢትዮጵያ