AMN- መስከረም 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በመላው ብሄሮች፤ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ወንድማማችነት እና አንድነት ላይ የተመሰረተች ኅብረ-ብሄራዊት ሃገር ነች፡፡
በኅብር የተመሰረተች፤ በኅብር ያጌጠች እና በኅብረ-ብሄራዊ አንድነት ላይ የተገነባች የብዙሃን መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖቶች፤ ቋንቋዎች፤ ባህሎች እና ማንነቶች የሚገኙባት እና በእኩልነት የሚኖሩባት የጥቁር ሕዝቦች እና የአፍሪካዊነት ልዩ ምልክትም ነች፡፡
ወንድማማችነት፤ አብሮነት፤ መከባበር፤ መቻቻል እና መተሳሰብ የሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦች እና የመላው ኢትዮጵያዊያን ትልቁ መገለጫና ባህልም ጭምር ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት ትልቁ የጥንካሬ ምስጢርም፤ ሃገሪቱ በሁሉም ሕዝቦች መልካም ፈቃድ፤ ወንድማማችነት፤ አብሮነት እና አንድነት ላይ የተመሰረተች ታላቅ ሃገር መሆኗ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አክብረው እና አንድነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ፤ ጽኑ የሃገር ፍቅር ያላቸው፤ በሃገራቸው ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ ከማንም ጋር የማይደራደሩ ጠንካራ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በኅብር እና በኅብረ- ብሄራዊ አንድነት በተገነባው ጠንካራ አንድነታቸው የውጭ ወራሪ ሃይሎችን ከመመከት እና የሃገራቸውን ሉዓላዊነት ከማስከበር ጀምሮ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን በጋራ በመገንባት የኢትዮጵያዊነትን የጥንካሬ ምንጭ ለተቀረው ዓለም አስተዋውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እና ህልውና ለመድፈር በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ የጦርነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም የመላው ብሄር፤ ብሄረሰቦችን እና ህዝቦችን ብርቱ ክንድ መመከት አልቻሉም፡፡
እነዚሁ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሃገሪቱን ሕዝቦች በብሄር እና በሃይማኖት ሽፋን ለማጋጨትና ደም ለማቃባት የተለያዩ ሴራዎችን ቢፈጽሙም በጽኑ ኅብረ-ብሄራዊነት የታጋመደውን የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰቦችን እና ሕዝቦችን ወንድማማችነት መበጠስ አልቻሉም፡፡
ይልቁንም ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በምክክርና በንግግር በመፍታት፤ የሰለጠነ አዲስ የፖለቲካ ባህል በመፍጠር፤ ጽንፈኝነትን፤ ዘረኝነትን፤ መከፋፈልንና እና ጥላቻን በማውገዝ እና ኅብረ-ብሄራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ትናንት እንደለመዱት ሁሉ በቅርቡ የተካሄደዉን 7ኛዉን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ቢጣጣሩም መላዉ የሃገሪቱ መራጮ ግን በነቂስ ወጥተዉ ድምጽ በመስጠት የጠላትን ሴራ አክሽፈዋል፡፡
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መከናወን ተከትሎም፤ አዲሱ የመደመር መንግሥት ዛሬ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም. በይፋ ይመሰረታል።
ይህም የዘመናችን አዲሱ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት የጥንካሬ ምስጢር ሆኗል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ