ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በባህር በር ዙሪያ ላይ ያላት ጽኑ አቋም በማንኛዉም ሁኔታ የማይቀየር መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተወቀ

AMN- መስከረም 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በባህር በር ዙሪያ ላይ ያላት ጽኑ አቋም በማንኛዉም ሁኔታ የማይቀየር መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ አስታወቀ፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ፣ በተለምዶ ብሉ ናይል ተብሎ የሚጠራው ምንጭ መሆኗን ገልጿል፡፡

ከብሉ ናይል የሚመነጨው ውሃ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሚመነጭ ሲሆን፣ አባይ ከአጠቃላይ የናይል ወንዝ ፍሰት ውስጥ ወደ 85 በመቶ የሚጠጋውን ያበረክታል።

ስለዚህ፣ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀምና አስተዳደር ጋር የተያያዘ ማንኛውም ውይይት እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች መነሻ ማድረግ ይገባዋል ይላል ሚኒስቴሩ በመግለጫዉ፡፡

በተመሳሳይም፣ ቀይ ባሕር ኢትዮጵያ በመልክዓ-ምድራዊም ሆነ በታሪካዊ መልኩ ትስስር ያላት የባሕር አካል ነው።

በጊዜ ሂደት የፖለቲካ ድንበሮች ለውጥ ቢያጋጥማቸውም፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ትስስር አሁንም ጠንካራ ነው፡፡

በቅርብ የሚገኘው የኢትዮጵያ ድንበርም ከባሕሩ ዳርቻ በ30 ማይል ያህል ብቻ ይርቃል።

በመሆኑም፣ ስለ ክልላዊ የባሕር ጉዳዮችና የደኅንነት ሥርዓት የሚደረግ ማንኛውም ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞችና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ትስስር ማጤን ይገባዋል::

እነዚህ መልክዓ-ምድራዊና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካዊ ንግግሮች፣ በማስገደድ እርምጃዎች ወይም በማተራመስ ድርጊቶች ሊቀየሩ አይችሉም ነዉ ያለዉ ሚኒስቴሩ ባወጣዉ መግለጫ::

በተወካዮች በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች በመሬት ላይ ያሉትን እውነታዎች አይቀይሩም፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞች፣ ሚና እና በክልሉ ያላትን ኃላፊነት አያሳንሱም።

ኢትዮጵያ ሰላማዊ ተሳትፎን፣ የጋራ መከባበርን እና ክልላዊ ትብብርን ማስቀጠሏን ትቀጥላለች ሲል ሚኒስቴሩ ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ዋና የሀገራዊ ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ዝግጁ ሆና ሳለ፣ ሁሉም የክልሉ ተዋናዮች የጋራ ችግሮችን በገንቢ ውይይት፣ በአጋርነት እና በመልካም ጎረቤትነት መርሆች መሠረት እንዲፈቱ ትጠይቃለች፤ ይህም ከግጭትና ከ“ዜሮ-ድምር” አቀራረቦች ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review